የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን የሪፎርም ሥራ ዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያ እና የአዲስ ሕንጻ ምረቃ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ በሙያ ብቃቱ የላቀ፣ በጀግንነት የሚሠራ እና በሰብዓዊነት የሚያገለግል የፖሊስ ተቋም ለመገንባት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል።
የአማራ ክልል ፓሊስ የሪፎርም ስራ በሁሉም ዘርፎች አመርቂ ውጤትን ማስመዝገብ የሚያስችል ሲሆን በወንጀል መከላከል ዘርፉ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚያስችል አሰራርን ያበሰረ ነው ተብሏል።
የተቋሙ ሪፎርም የተጀመረውን የህግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል እና በአጭር ጊዜ ወደ ቀደመ ሰላሙ ለመመለስ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን በመርሐ ግብሩ ተጠቁሟል።
የተመረቀው አዲሱ ባለ ሰባት ወለል ሕንፃ ማስፋፊያ ደረጃውን የጠበቀና ለወንጀል ምርመራ ስራ አጋዥ የሆኑ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ያሟላ እና የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብት በጠበቀ መልኩ የምርመራ ክፍሎችን ያካተተ ነው።
በዛሬው የሪፎርም ሥራዎች ዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያ እና የአዲስ ሕንጻ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ፣ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ፣ የአማራ ክልል ዋና አፈጉባኤ ክብርት ፋንቱ ተስፋዬ፣ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኀላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሸነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ.ር)፣ ምክትል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የቢሮ ኃላፊዎች፣የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የጦር አዛዦች፣ የክልሉ ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ ስታፍ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።
