“ያለ ሕግ ዘላቂ ሰላምን መገንባት አይቻልም” አቶ ዓለምአንተ አግደው

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ”የጋራ ርዕይ ለጠንካራ የዳኝነት አገልግሎት” በሚል መሪ መልዕክት ከፍርድ ቤት ዳኞች እና ከጉባዔ ተሿሚዎች ጋር ለአሥር ቀናት የሚቆይ ጉባዔ ጀምሯል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የጉባዔው ዓላማ ዳኞች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል የሕዝብ አመኔታ ማግኘት በሚቻልበት ኹኔታ ላይ ለመምከር ነው ብለዋል።

በፍርድ ቤት ሥራዎች፣ ግንኙነቶች እና ሕጎች ላይ በመወያየት እና ግልጽነት በመያዝ ለሥራዎች ምቹ ኹኔታ መፍጠር ያለመ መኾኑንም አንስተዋል።

ያለ ሕግ ዘላቂ ሰላም እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንደማይቻል የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ለሕግ ትኩረት ሲሰጥ ሕግና ሥርዓት እንደሚከበርም ገልጸዋል።

ሕግ ሲከበር መልካም አሥተዳደርን በማስፈንም ውጤታማ ልማት ማምጣት ይቻላል ብለዋል።

ፍርድ ቤቶች ሁለንተናዊ ልማትን ለማፋጠን ዋስትና መኾናቸውን እና መልካም አሥተዳደር ለማስፈንም ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የፍርድ ቤቶችን ሚና በአግባቡ የማይገነዘቡ አካላት መኖራቸውንም አንስተዋል። ይህንን በማስተካከል የማኅበረሰብ ተስፋነታቸውን ማሳወቅ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የተገልጋዮችን እርካታ እና የሕዝብን አመኔታ ያረጋገጠ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት ቅቡልነት ያላቸው የዳኝነት አካላትን ለመፍጠር እንቅፋቶችን መቅረፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል። በተሠሩ ሥራዎች ውጤት እየታየ መኾኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት በ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅዱ እና በ5 ዓመት ስትራቴጅክ እቅዱ ለፍርድ ቤቶች ትኩረት በመስጠት ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።

የማስቻያ ቦታ እና ሌሎች ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የክልሉ ሕዝብም የዳኝነት ሥርዓቱን ለማሻሻል ለሚደረገው ርብርብ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ጥቂት ለብልሹ ሥነ ምግባር የተጋለጡ ባለሙያዎችን በማስተካከል የፍርድ ቤቶችን ተዓማኒነት እና ተቀባይነት ለማረጋጥ አፋጣኝ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ፍትሕን ተደራሽ ለማድረግ እና ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ተናግረዋል። ለባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን እውቅና መሰጠቱንም አንስተዋል።

የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ትብብርን ማጠናከር በተያዘው በጀት ዓመት በትኩረት እንደሚሠራበት ገልጸዋል።

የለውጥ ሥራዎችን በማጠናከር የዳኝነት አሰጣጡን ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ አካላት በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል።

የዳኞች ጉባኤ በለውጥ ፕሮግራሞች እና አዳዲስ ሕጎች ላይ ግንዛቤ በመያዝ ፍትሕን ለማስፈን አቅም እንደሚኾንም አመላክተዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top