ምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)
በአማራ ክልል በ2017 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት መርኃ ግብር በዛሬዉ እለት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ ላይ ተገኝተዉ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) እንደተናገሩት ‹‹በላቀ ትጋት ፤ ትኩረት ሰጥታችሁ የላቀ ውጤት ያስመዘገባችሁ የፅናትና የታታሪነት አብነት የሆናችሁ ጀግኖች ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ›› በማለት ልባዊ ደስታቸዉን አስተላልፈዋል ፡፡
ዛሬ በታላቅ ኩራት ነገን በተስፋ የምንጠበቅበት የመነቃቃት ቀን ነዉ ሲሉም ገልጸዋል ።
ታላላቅ ስኬቶች በታላላቅ ፈተናዎች ውስጥ ይወለዳሉ፤ የእናንተ ውጤትም ችግርን የማሸነፍ እሳቤ ነው፤ ስኬታችሁ ከግለሰብ በላይ ነው ያሉት ክቡር ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ትምህርት የሀገር እድገትና ብልፅግና መሰረት ፤ የፈጠራ በሮች የሚከፈቱበት ቁልፍ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
የዛሬ ተሸላሚ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢ ትዉልዶች ናቸዉ ፤ የዛሬ ስኬትና ዉጤት የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የመምህራኖች፣ የወላጆች ፣ የትምህርት አመራሩ እና የመላዉ ማህበረሰብ የጋራ ስራ የቅንጅት ዉጤት ነዉ ብለዋል ፡፡
ብዘኃ ችግርና ቀውስ ባለበት ዘመን ትምህርት ማኅበረሰብን ከችግር የሚያወጣ እና የሚያሻግር ዘላቂ መንገድ መሆኑን በመገንዘብ የክልሉ መንግሥትም የአንድ ትውልድ ዘመን ሕልም እና ርዕይ ቀርጾ የላቀ ሰብዓዊ ልዕልናን ለማረጋገጥ አስተሳስሮ እየሠራ ይገኛል ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የአማራ ክልል መንግሥትም ትምህርት የሀገር ግንባታ መሠረት መሆኑን በመረዳት በቀጣይም እንደ ክልል ከሌሎች ዘርፎች በማስተሳሰር ለትምህርት ዘርፉ በልዩ ሁኔታ ያልተቋረጠ ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የአማራ ክልልን የነገ ብልጽግና እና ዕድገት ለማረጋገጥ ዛሬ ላይ የወጣቶችን የትምህርት ልማት በላቀ ደረጃ መምራት ይገባልም ብለዋል።

