የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅዱ የግጭት እና ድህነት አዙሪትን በዘላቂነት የሚፈታ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
“አርቆ ማየት፣ አልቆ መሥራት” በሚል መሪ መልእክት በአማራ ክልል በተዘጋጀው አሻጋሪ የዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ዙሪያ ለክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ተከታታይ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
ከነሐሴ 18/2017 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም ለከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ሲሰጥ የሰነበተው ሥልጠና ተጠናቅቋል።
በማጠናቀቂያ መርሐ ግብሩ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ መልእክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅዱ ዋነኛ ዓላማ በክልሉ ውስጥ የሚስተዋለውን ድህነት እና ግጭት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ዕቅዱ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ ተከፋፍሎ የሚተገበር እና ትውልዶች እየተቀባበሉ ከዳር የሚያደርሱት መኾኑን ገልጸዋል።
ግጭት እና ድህነት አንዱ ሌላውን እየወለደ እና እየተመጋገቡ እንዲቀጥሉ መፍቀድ የለብንም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በኢኮኖሚ የበለጸገ እና በሰላም የሚኖር ሕዝብ መፍጠር ከዘመኑ መሪዎች የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር መኾኑን አስገንዝበዋል።
መሪዎች በክልሉ ያለውን ሥር የሰደደ ድህነት እና ግጭት ለመቅረፍ ከምንጊዜውም በላይ መትጋት እና መስዋዕትነት እስከመክፈል ድረስ ተቆራርጠው መሥራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የተዘጋጀውን አሻጋሪ የዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የመሪዎች ቁርጠኝነት በእጅጉ ያስፈልጋል፤ የሕዝቡ ተሳትፎም የማይተካ ሚና አለው ነው ያሉት።
በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ እና በአግባቡ በመጠቀም ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ማመንጨት ለነገ የሚተው ሥራ እንዳልኾነም አመላክተዋል።
“ሕዝባችን ከድህነት መውጣት ብቻ ሳይኾን በቅንጦትም የመኖር ፍላጎት አለው፤ ይገባዋልም” ነው ያሉት።
እንደሀገር እና እንደክልል ያለንን እምቅ ሃብት በአግባቡ በመለየት እና በመምራት መሥራት ከተቻለ ሕዝባችንን ከድህነት ማውጣት ብቻ ሳይኾን እንደየፍላጎቱ በቅንጦት እንዲኖር ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
ዕቅዱ ክልሉ ያለውን ጸጋ የለየ፤ በትብብር የሚፈጸም እና ሁሉንም በቁጭት ወደልማት የሚያስገባ መኾኑንም ተናግረዋል። በአሁናዊ ሁኔታዎች ተሰላችቶ እጅን አጥፎ መቀመጥ ለውጥ እንደማያመጣም አስገንዝበዋል።
በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች እና ሕዝቡ በጋራ በመቆም እና በመናበብ ይህንን የትውልድ ዕቅድ በጋራ መፈጸም እና በጋራ ከፍ ማለት ይገባል ነው ያሉት።
በድህነት እና ጦርነት አዙሪት ተዘፍቀው የነበሩ ሀገራት ከችግራቸው ተምረው እና አሻጋሪ ዕቅድ አቅደው ከመሪዎቻቸው ጋር በመሥራት ችግራቸውን አልፈውታል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አሁን ላይ የዓለም ቁንጮ ለመኾን በቅተዋልም ብለዋል።
እኛም ከዓለም ተምረን እና እንደየተጨባጭ ሁኔታዎቻችን ችግሮቻችንን ፈትተን በጋራ መቆም እና በዕቅድ ተመርተን መሻገርን ባሕል ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
የግጭት እና ድህነት አዙሪት መዘጋት አለበት፤ ቴክኖሎጅን በመጠቀም የተሳለጠ ሥራ ማከናወን እና ገና ያልነካናቸውን አቅሞች ሁሉ ፈልገን በመጠቀም መልማት አለብን ብለዋል።
ትምህርት ዋነኛ የመወዳደሪያ መሣሪያችን በመኾኑ በትኩረት የምንሠራው መኾን አለበት ነው ያሉት። የታቀደው ዕቅድም ለትምህርት፣ ሥልጠና እና ለቴክኖሎጂ ትኩረት የሰጠ መኾኑን ተናግረዋል።
የተማረ እና ቴክኖሎጅን የታጠቀ ዜጋ ለታሰበው ለውጥ መሠረት መኾኑንም አብራርተዋል።
በአሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅዱ ዙሪያ ተከታታይ ሥልጠናዎችን የወሰዱ መሪዎች ያገኙትን ዕውቀት እና ክህሎት በየደረጃው በማውረድ መተግበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ዕቅዱን በውል መረዳት፣ ለሌሎችም ማስረዳት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።ዕቅዱ የልማት እና የመለወጥ ነው፤ ባለቤቱም ሕዝብ ነው ብለዋል።

