(ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም) በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ፕሮግራሙ በክልሉ ላለፉት 20 ዓመታት ሲሠራበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በተተገበረው ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በገንዘብ ድጋፍ እና በብድር አገልግሎት አማካኝነት የተጠቃሚዎችን ምርታማነት ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ የሴፍቲኔት ልማታዊ መርሐ ግብሩ በክልሉ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሲደረግ የነበረውን ጥረት በመደገፍ በኩል የራሱ ድርሻ ነበረው ብለዋል፡፡
ተጠቃሚዎች ከጊዜያዊ ድጋፍ ባለፈ ከተረጅነት ራሳቸውን በማላቀቅ ቋሚ ጥሪት ማፍራት እንዲችሉ ፕሮግራሙ ማገዙን ጠቅሰዋል፡፡
ከ196 ሺህ በላይ የቤተሰብ ኀላፊዎች በሥራቸው ከ630 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች ያሏቸው ናቸው፤ በፕሮግራሙ ሲታገዙ ቆይተው መመረቃቸው ነው ቢሮ ኀላፊው የገለጹት፡፡
በክልሉ ያለውን ጸጋ አሟጦ በመጠቀም በመንግሥት እና በአጋር ድርጅቶች ለተጠቃሚዎች ይደረጉ የነበሩ ድጋፎችን በአግባቡ መጠቀም በመቻሉ ዛሬ ላይ ለማስመረቅ በቅተናል ብለዋል፡፡
ክልላዊ የልማት ሴፍቲኔት ፕሮግራም 5 በክልሉ፣ 11 ዞኖች፣ በ87 ወረዳዎች ላይ 1 ሺህ 823 ቀበሌዎች ውስጥ እየተተገበረ መሆኑን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡
በውስጥ አቅም እና የባለድርሻ አካላትን እገዛ በመጠቀም ክልሉ የጀመረውን ከተረጅነት ወደ ምርታማነት የማሸጋገር ጉዞ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ በመርሐ ግብሩ አማካኝነት በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በተፍሰስ ልማት እና በመስኖ ልማት ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት የተጠቃሚዎችን ሕይወት በቋሚነት እንዲለወጡ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ዘላቂ ልማትን በሚያረጋግጥ መንገድ የዜጎችን ምርታማነት የሚያጎለብቱ ሥራዎች በውጤታማነት ማከናወን እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

