ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ሕዝብ በሥርዓተ መንግሥት ምስረታና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን እህት ወንድም ሕዝቦች ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ አንድነት አወንታዊ ድርሻዉን የተወጣ ሕዝብ ነው።

ሕዝባችን በርካታ አኩሪ ታሪኮች ያሉት፤ ከክልሉ ባለፈ የሀገራችን ሕዝቦች ቋንቋቸው፣ ሃይማኖታቸው እና ማንነታቸው ተከብሮ፤ በመቻቻልና በአብሮነት እንዲኖሩ የሠራ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡

ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታትም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተከብረውለት በነፃነት እንዲኖር በተካሄደው የለውጥ ጉዞ የክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ የሚታወቅ ሃቅ ነው፡፡

በተለይም በተሳሳተ ትርክት ሕዝባችንን ዋጋ ሲያስከፍሉ የቆዩ ግፈኞችን ከሌሎች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በጋራ ታግሎ በሀገራችን ታሪካዊ ለውጥ እንዲመጣ የታገለ ሕዝብ ነዉ፡፡

በሂደቱም ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም ሌሎች የለውጡ መሪ የነበሩ ኃይሎች ድርሻቸዉ በታሪክ የሚቀመጥ ነው።

በሀገራችን የተገኘዉን ለውጥም በለውጥ ፈላጊ ኃይሎች የተባበረ ክንድና በሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ ማስቀጠል ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ለውጡን ለማፅናት እና ለማስቀጠል መንገዶቹ ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩም። ከለውጡ ጅማሮ አንስቶ የመንግሥትን ሆደ ሰፊነት እንደ ፍርሃት በመቁጠር ሕዝባችን ያገኘዉን ሁለንተናዊ ድል ለመቀልበስ መልከ ብዙ ፈተናዎችና ጠመዝማዛ መንገዶች ታልፈዋል፡፡

በሴራ ፖለቲካ ተወልደው ያደጉ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ባዕዳን በመቀናጀት ሀገራችንንና ክልላችንን በጦርነት ለማመስ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም ብሎ በድፍረት መግለጽ ይቻላል፡፡

በተለይ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልላችን ፅንፈኛ ቡድኖች የአማራን ሕዝብ ትክክለኛ ጥያቄዎች እንደሽፋን በመጠቀም ወደ ግጭት በመግባት በሕዝብ ላይ ከባድና አሳፋሪ ሰባዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሰዋል፡፡

ይህ ቡድን የሕዝብ መጠቀሚያ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፤ የነገ ሀገር ተረካቢ ትዉልድ እንዳይኖር የትምህርት ሥርዓቱን አስተጓጉሏል፤ መምህራንን ገድሏል፤ የሚማሩ ህጻናት ላይ ቦምብ በመጣል ጉዳት አድርሷል፤ ከራሱ ሃሳብ ጋር አልሄዱም ያላቸውን ሁሉ በሃሳብ ልዩነት ብቻ ረሽኗል፤ የሀገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን ገድሏል፤ ሰው የሆነ ፍጡር ያደርገዋል ተብሎ የማይታሰብ ድርጊት በጭካኔ እጅ እና ጆሮ በመቁረጥ የአረመኔነቱን ጥግ በአደባባይ አሳይቷል፣ ትርፍ አምራቹ አርሶ አደር ያመረተዉን ለገበያ እንዳይሸጥ እና ግብአት እንዳይቀርብለት ከልክሏል፤ የምርትና አገልግሎቶችን እንቅስቃሴ ገድቧል፣ እገታ እና መሰል የሽብር ተግባራትንም በስፋት ፈፅሟል።

ይህ የሽብር ተግባር የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን በተቀናጀ መልኩ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ክልሉን በልዩ ልዩ የሴራ መንገዶች ማዳከም በሚል የሚከተለው እቅድ መሆኑ በግልፅ ሁሉም ሊገነዘበውና ሊታገለው ይገባል፡፡

ይህንን አፍራሽ እቅዱን ለማሳካት ጦር መሣሪያ በማስታጠቅ፣ ወታደራዊ ድጋፍ በመስጠት፣ በፕሮፖጋንዳ በማገዝ፣ በፋይናንስና በሚዲያ በመደገፍ በተቀናጀ መልኩ ታስቦበት የተሠራና የአማራን ሕዝብ መሪ አልባ እንዲሆንና አንድነት እንዳይኖረው በማድረግ እርስ በርሱ እንዲባላ የተሸረበ እኩይ ሴራ ነው፡፡

ይሄን እኩይ የፅንፈኞች ድርጊትና ተግባር ለመቀልበስም መንግሥት ከታታሪው፣ ከአርቆ አሳቢውና ከሰላም ወዳዱ የክልላችን ሕዝብ ጋር በመሆን በወሰደዉ ሕግ የማስከበር እርምጃ የፅንፈኞችና የላኪዎቻቸውን ህልም በማክሸፍ ሕዝባችን የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል።

ክልሉን በሁሉንተናዊ መልኩ የማዳከም ፕሮጀክት ያላቸው ባንዳዎችንና ባዕዳንን የፌደራልና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በቅንጅት አስፈላጊውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ውድ የሆነውን ሰላም በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ አንፃራዊ ሰላም እንዲመጣም የጥምር ፀጥታ ኃይላችን አኩሪ ገድል በታሪክ ሲዘከር የሚኖር ነው፡፡

ስለሆነም ከምንም በላይ የተጀመረውን የልማትና የብልፅግና ጉዞ ለማስቀጠልና የአማራን ሕዝብ ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ከምንጊዜውም በላይ ርብርብ እንደሚያደረግ፤ አክራሪነትና ፅንፈኝነት ለራሱ ለፅንፈኛውም የማይበጅና የተሸናፊዎች መንገድ በመሆኑ ችግሮችንም በውይይትና በሰላም ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ምንጊዜም ለሰላም የዘረጋዉ እጁ የማይታጠፍ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ታጥቀው ጫካ ሲንንቀሳቀሱ የነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሃይሎችም የክልሉን መንግሥት የሰላም ጥሪ ተቀብለው በመግባት እና ወደ ኅብረተሰቡ በመቀላቀል መደበኛ ሕይወታቸዉን እንዲመሩ ማድረግ ተችሏል። ይሄ የሰላም ጥሪ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑንም ለማሳወቅ እንወዳለን።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተጠናክሮ የቀጠለው የፅንፈኞች ተግባር ለአማራ ሕዝብ ከፍተኛ በደል እያስከተለ መሆኑንና ታጣቂው ከአማራ ሕዝብና ከኢትጵያ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት ሀገር ለማፍረስ በተላላኪነት እያገለገለ መሆኑን የተረዱ ወጣቶችና ቡድኖች መንግሥት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ እየተቀበሉ ነው፡፡

በተለይ ደግሞ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ዝግጁነት ውጤት ነው፡፡

መንግሥታችን የገጠሙትን ፈተናዎች ሁሉ ተጋፍጦና ተቋቁሞ እንደ ክልል በልማት፣ በሰላምና በልዩ ልዩ ተግባራት በተለየ እምርታዊ ጉዞ ውስጥ ለመግባት ጥረትም አድርጓል፡፡

ተጨባጭ ለውጥም ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የክልሉ መንግሥት የአጭርና የረዥም ጊዜ ስትራቴጅክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደሥራ በመግባት፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በሳይንስና ቴክኖሎጅ ዘርፎች ዕምርታዊና ተመጋጋቢ ዕድገት በገጠርና በከተማ ለማስመዝገብ ዓልሞ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

በትምህርትና በጤናው ዘርፍም የላቀ ለውጥ ለማምጣት ክፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በግጭት ምክንያት ተስተጓጉለው የነበሩ ትምህርት ቤቶችም ተከፍተው ተማሪዎቻቸውን በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡

እየተመዘገቡ ያሉ ተስፋ ሰጭ የልማት ውጤቶችም አሉ፡፡ የከተሞች የኮሪደር ልማት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በበጋ ስንዴ ልማት፣ የስሚንቶ ፋብሪካዎች— ወ.ዘተ. በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ከሥራ አጥነት እና ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዘው ከሕዝባችን የሚነሱ ችግሮችንም ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአገልጋይነት መንፈስ ጠንክረን እየሠራን እንገኛለን።

በአጠቃላይ መንግሥት የሕግ ማስከበሩን ተግባር አጠናክሮ ከማስቀጠል ጎን ለጎን የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ይበልጥ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሰላማዊ ውይይቶች ችግሮችን የመፍታት አማራጭን በመከተል ልማትንና ጥራት ያለው የሕዝብ አገልግሎት አሠጣጥ ሥራዎችን ለማስቀጠል በከፍተኛ ትኩረት የሚሠራበት ጉዳይ ይሆናል፡፡

በመሆኑም ዘላቂ ሰላምን እና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ሕዝቡ ፅንፈኞችንና ተላላኪወችን የሚሸከምበት ትክሻ እንደሌለው በተደረጉት ትልልቅ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ያሳየበትን አቋሙንና የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እናቀርባለን፡፡

አሁንም ድረስ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ወደጎን በመተዉ የክልላችንን ሰላም ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ሃይሎችን የማንታገስና የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የሆነዉን ሕግ የማስከበር ተግባር አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑንም ለማሳወቅ እንወዳለን።

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በሀሰተኛ መረጃዎች ሳይደናገሩ በሀገራችንና በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የማይቀረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ በምናደርገው ርብርብ የበኩላቸውን አወንታዊ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top