በእንስሳት ማድለብ ሥራ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች እና ግለሰቦች የተሟላ የማድለብ ሂደትን ተከትለው እንስሳትን ለገበያ በማቅረብ ትርፋማ እንዲሆኑ እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት መምሪያ አስታውቋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ በልስቲ ሹመት (ዶ.ር)፦ በተደረገው ሙያዊ የክትትል እና ድጋፍ ሥራ በዘርፉ የተሰማሩ ማኅበራት እና ግለሰቦች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ከ6 ሺህ በላይ የደለቡ ከብቶችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ገበያ ለማቅረብ እየሠሩ መኾኑን አስገንዝበዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ 22 ኢንተርፕራይዞች፣ ግለሰቦች እና ባለሃብቶች በየጊዜው ከባለሙያዎች የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ተከትለው በማርባት እና በማድለብ ውጤታማ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡
በከተማው የእንስሳት ሃብት ልማትን በዘመናዊ መልኩ ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ለእርድ የሚኾኑ በጎችንም ወደ ተጠቃሚዎች ለማቅረብ በስፋት መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡
የዶሮ እና የወተት ምርቶችንም በኅብረት ሥራ በተደራጁ ማኅበራት አማካኝነት በተለያዩ አካባቢዎች በአንድ ማዕከል በቅርበት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ እንዲቀርብ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
እንስሳትን በማድለብ ሥራ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች እና ግለሰቦች ላለፉት ሦሥት እና አራት ወራት ለእንስሳት ተገቢ ክትትል በማድረግ እና በአግባቡ በመንከባከብ የተሻለ ዋጋ የሚያወጡ የዳልጋ ከብቶችን ለገበያ በማቅረብ ትርፋማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተቋሙ የሚደረግላቸው ሙዊ ድጋፍ እና ክትትል ለውጤታማነታቸው አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው የተናገሩት፡፡
ኢንተርፕራይዞች በቀጣይም የገንዘብ አቅማቸውን በመጨመር በዘርፉ የበለጠ ውጤታማ ለመኾን አቅደው እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግም የማኅበረሰቡን ፍላት ለማሟላት ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የእርድ እንስሳትን ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን መናገራቸውን ከእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

