(ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም) የኮሪደር ልማት የአንድን ከተማ መንገዶችን እና የመንገድ ዳርቻዎችን መነሻ በማድረግ በታቀደ እና በተቀናጀ መልኩ ከተማን የማዘመን ሥራ ነው።
ይህም የከተማን ውበት ይጨምራል፣ የቱሪስት መስህብነትን ያሳድጋል፣ የንግድ እንቅስቃሴን ያሳልጣል፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችንም ይፈጥራል።
የብስክሌት እና የእግረኛ መንገዶችን በማስተካከል የትራፊክ ፍስሰትን ያቀላጥፋል። ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ያበረታታል።
ከተማን ዘመናዊ፣ ውብ እና ፅዱ በማድረግ ለነዋሪዎች ምቹ እንዲኾኑ የሚያስችል የከተማ የልማት ስልት ነው።
በአማራ ክልል የኮሪደር ልማት ከሚያከናውኑ ከተሞች መካከል የደሴ ከተማ አንዷ ናት።
ደሴ ከጥንታዊ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ ብትኾንም የሚገባትን ያህል የመሠረተ ልማት ሳይሟላላት መቆየቷን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ይገልጻሉ።
አቶ ሳሙኤል እንደገለጹት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የልማቱ ተቋዳሽ እየኾነች መጥታለች።
በቅርቡ በተጀመረው የኮሪደር ልማት መርሐ ግብር በከተማዋ ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አስታውቀዋል።
የከተማዋ መልከዓምድራዊ አቀማመጥ፣ ነባር የአስፋልት መንገዶች አለመኖር እና ከፍተኛ የልማት ተነሽዎች መኖራቸው ለኮሪደር ልማቱ ጫናን አሳድሮ እንደነበር አንስተዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ለችግሮች ሳይበገር የተለያዩ መፍትሄዎችን በማስቀመጥ የኮሪደር ልማት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም አዳዲስ የአስፋልት መንገዶችን መገንባት፣ ለልማት ተነሽዎች የቦታ ትክ ቀድሞ ማዘጋጀት እና የልማት ድርጅቶችን በማቋቋም ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል።
ለአብነትም በከተማ ምክር ቤት ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጭ መቋቋሙን እና የመንገድ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት መደራጀቱንም አንስተዋል።
ሁለቱን ድርጅቶች በመጠቀም የኮሪደር ልማቱን እና የአስፋልት መንገድ ግንባታ በራስ አቅም ለማከናወን መቻሉን አስረድተዋል።
ይህም በዝቅተኛ ወጭ፣ በጥራት እና በፍጥነት በማከናወን ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበበት እና ለሌሎችም ተሞክሮ የሚኾን ነው ብለዋል።
ለልማት ተነሽዎች ቦታ በመስጠትም የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዳይፈጠሩ መደረጉን አመላክተዋል።
በመጀመሪያው የኮሪደር ልማት በተለምዶ ከቧንቧ ውኃ እስከ ወሎ የባሕል አምባ ድረስ በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ተናግረዋል።
ሁለተኛውን የኮሪደር ልማትም እስከ የካቲት 30 ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከከተማዋ ስፋት አንጻር የተሠራው የኮሪደር ልማት በቂ አለመኾኑን ገልጸው የአስፋልት መንገዶችን ጭምር በመገንባት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ልማትን ለማምጣት ሰላም መሠረታዊ ነገር ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል መሪዎች፣ የጸጥታ መዋቅሩ እና ሕዝቡ በጋራ በመሥራቱ ከተማዋ በአስተማማኝ ሰላም ላይ ትገኛለች ነው ያሉት ። በቀጣይም ሰላምን በማጽናት የልማት ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።

