“የሃይማኖት አባቶች አስታራቂ ሚናቸውን መወጣት አለባችሁ” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

(ታሕሳስ 17/2018 ዓ.ም) “ዘካሪ መካሪ የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከሰሜን ጎጃም ዞን የሃይማኖት መሪዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ተወያይተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በማኅበረሰቡ ዘንድ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት የሃይማኖት አባቶች የእውነት፣ የፍትሕ እና የእርቅ ጠባቂ ተደርገው እንደሚወሰዱ ገልጸዋል።

የሃይማኖት አባቶች ሰላምን አብዝቶ የሚሻ፣ የግብረ ገብ እና የሥነ ምግባር ጠባቂ፣ ችግር ባጋጠመ ጊዜ ደግሞ አረጋጊ ተደርጎ ይቆጠራል ነው ያሉት።

የዘላቂ ሰላም ግንባታ የሃይማኖት አባቶችን ተሳትፎ እና አበርክቶ ይሻል ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች የማይሳተፉበት የሰላም ግንባታ እና የግጭት አፈታት ሂደት ውጤታማ እንደማይኾንም አንስተዋል።

አሁን እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታትም የሃይማኖት አባቶች ሀቀኛ አበርክቶ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከሃይማኖት አባት የሚጠበቀው ሰላምን እና ፍቅርን መከተል፣ ምዕመናን ሰላምን እንዲከተሉ ማድረግ እና ችግር ሲያጋጥም ደግሞ የመምከር ሚና መጫወት ነው ብለዋል።

በሕዝቡ ላይ ያላችሁን የመንፈሳዊነት፣ የሥነ ምግባር እና ግብረ ገብ የበላይነትን በመጠቀም ስለ ሰላም አስተምሩ ነው ያሉት።

ከሽማግሌዎች ጋር በመቀናጀት እና በመደራጀት ታጣቂ ኃይሎች በሰላም እንዲገቡ የማሸማገል ሥራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በማኅበረሰቡ ላይ የደረሰውን መከራ በሚገባ በመረዳት “የሚጠበቅባችሁን አባታዊ እና ሃይማኖታዊ ሚናችሁን መወጣት ይገባችኋል” ነው ያሉት።

በመንግሥት እና በሕዝቡ መካከል ድልድይ ኾናችሁ መካሪ ዘካሪ ሁኑ ብለዋል።

ለሰላም ግንባታ “የሃይማኖት አባቶች እውነተኛ እና ጠንካራ የአስታራቂ ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸው” አሳስበዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን ሰላምን የሚያመጣው መንግሥት ብቻ አይደለም ብለዋል።

ችግሩን በውይይት እና በሽምግልና ለመፍታት የሃይማኖት መሪዎች ከፍ ያለ ሚና እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ለመመካከር እና ለመግባባት የሃይማኖት መሪዎች ግንባር ቀደም ኾነው የበኩላቸውን የመሪነት ሚና መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

የሃይማኖት ተቋማትም በጫካ ላሉት ኃይሎች መሸሸጊያ መኾን የለባቸውም ብለዋል።

ችግሮች በጠረንጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ መካሪ፣ አስታራቂ እና አቀራራቢ መኾን እንደሚገባቸው አንስተዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማስተዋል አሰሙ በጫካ ያለው ኃይል ትውልዱ ትምህርት እንዳይማር እያደረገ፣ ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር አብሮ እየሠራ፣ ንጹሀንን እየገደለ፣ ሕዝብን የበደለ በመኾኑ አምርሮ መታገል ይገባል ብለዋል።

ሁከት፣ ግጭት፣ ብጥብጥ እና ጦርነት እንዲበቃ የሃይማኖት አባቶች ቁርጠኛ በመኾን በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top