(ታህሳስ 16/2018 ዓ.ም ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር ፣ አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን እና 11ኛ መደበኛ ጉባዔ በመጀመሪያ ቀን ውሎው የክልሉ ትምህርት ቢሮ የአምስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።
በመድረኩ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አረጋ ከበደ ተገኝተው በተነሱት የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ ትምህርት ከሁሉም የልማት ዘርፎች በተለየ ሰብዓዊ ሀብት ልማት ላይ የሚሰራ በመሆኑ መሪ የልማት ስራ ነው ሲሉ ተደምጠዋል ።
የትምህርት ዘርፉ ከፀጥታ ችግሩ ጀርባ በጥራቱም በሽፋኑም ቀደም ብሎ ችግሮች የነበሩት ዘርፍ ነው ያሉት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አረጋ ከበደ ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበትና አብዛኛውን ጊዜ ትምህርት ሽፋን እንጅ ጥራት ትኩረት መነፈጉን አውስተዋል።
የትምህርት አሰጣጡም ገበያ መር ሆኖ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል።
ለዚህም የት/ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ልዩ ትኩረት ሰጥተን በተለይ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በመገንባት፣ የመፅሐፍ ተማሪ ጥምርታን በማስተካከል ፣ እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን በማሟላት መስራት ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል ።
ክቡር አቶ አረጋ ከበደ በጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ በመገንባት ወደ ትምህርት ያልተመለሱ ልጆቻችንን ለመመለስ ሁላችንም ርብርብ ማድረግ አለብን ሲሉም አሳስበዋል።

