በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በሁሉም ወረዳዎች የቡና ልማት በስፋት የሚለማበት አከባቢ ነው።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና ምክትል መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ስማቸው እንደገለፁት፦ የአዊ ብሔረስብ አስተዳደር ለቡና ልማት ምቹ አከባቢ በመሆኑ ከ4 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በቡና ችግኝ የተሸፈና መሆኑን ጠቅሰው የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 262 የቡና ክላስተር መኖሩን ተናግረዋል፡፡
የብሔረስብ አስተዳደሩ ቡና በሀገር አቀፍ ደረጃ በጥራትና በጣዕም የብራንድነት ስያሜ የተሰጠዉ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አዲሱ በተያዘው በጀት ዓመት 20 ሺህ ኩንታል ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅርብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቡና ልማት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ 2 ሚሊዮን 680 ሺህ ቡናና ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬ በመጪው ክረምት ለተከላ ለማዘጋጀት እየሰሩ መሆኑን ያብራሩት ምክትል ኃላፊው ፦ በአንዳንድ አካባቢዎች የቡና አድርቅ በሽታ እየተከሰተ በመሆኑ የምርምር ተቋማት በሽታውን በምርምር ለይተው ለመከላከል እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ቡናን በስፋት በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን በቡና ልማት ከተሰማሩት አርሶ አደሮች መካከል እንዳለው አያሌውና አዳነ ኃይሉ ተናግረዋል።
የቡና ልማት የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደረጋቸው በመሆናቸው ልጆቻቸውን በማስተማር ለደረጃ ከማድረሳቸው ባሻገር የቤተሰብን ህይወት እየቀየረ መሆኑን እርሶ አደሮች ገልፀዋል።
የቡና ልማት ቋሚ ሀብት ለልጅ የሚተላለፍና የተሻለ የገቢ ምንጭ በመሆኑ በስፋት ለማልማት እየሰሩ መሆኑንም አርሶ አደሮች ጨምረው መናገራቸውን ከአዊ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

