“ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ግፍን ማውገዝ እና ሐቅን መናገር ያስፈልጋል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

(ታሕሳስ 15/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ጎጃም ዞን ከመራዊ ከተማ አሥተዳደር እና ከሰሜን ሜጫ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የመራዊ ከተማ በታጣቂ ቡድኑ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት አንደኾነ ገልጸዋል። በአስቸጋሪ የጸጥታ ችግር ውስጥ መቆየቷንም ተናግረዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ለማስመሰል የሕዝብን ጥያቄ ያነሳ ነገር ግን ሕዝብን እየበደለ ያለ ጫካኝ ቡድን ነው ብለዋል።

ቡድኑ የዘራፊዎች እና የነፍሰ ገዳዮች ስብስብ መኾኑንም ተናግረዋል። መዳረሻ ግብ እና ዓላማ የሌለው ሕዝብን የሚያሰቃይ እንደኾነም ገልጸዋል።

ሰላምን የሰበኩ አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን የገደለ፣ ያዋረደ እና ያፈነ ቡድን ነው ብለዋል።

ጽንፈኛው ቡድን በመራዊ ከተማ እናት እና ልጅን በግፍ መግደሉንም አንስተዋል። ይሄን እያየን ልክ አይደለም ብለን ካልተነሳን ከጥፋት አንድንም ብለዋል።

መምህራንን በግፍ ያሰቃየ፣ ከልጆቻቸው ፊት መምህራንን አንበርክኮ የገደለ፣ ተማሪዎች እንዳይማሩ የከለከለ በግልጽ የሕዝብ ጠላትነቱን ያሳየ መኾኑን ገልጸዋል።

ታጣቂው ቡድን በመንግሥት ሠራተኞች፣ በወጣቶች እና በሌሎች ነዋሪዎች ውስጥ ቀኜ የውስጥ አርበኛ ብሎ የሰየማቸው መረጃ የሚያቀብሉ፣ ሰዎችን የሚያሳግቱ፣ የሚያስገድሉ እና የጭካኔ ተግባር የሚያስፈጽሙ ኃይሎች አሉ ብለዋል።

ቀኜ የተባለው ቡድን ሕዝብ እና መንግሥት እንዲለያዩ የሚያደርግ፣ የከተማ ላይ አመጽ ለማስነሳት የሚሠራ ቡድን መኾኑንም ገልጸዋል።

ቀኜ የሚባለውን ቡድን በተጠና ኦፕሬሽን ማጽዳት እንደሚገባ አንስተዋል።

መሪዎች መጀመሪያ የራሳቸውን ዘመድ መመለስ አለባቸው ነው ያሉት። ግጭቱ እንዲባባስ የሚሠሩ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች መኖራቸውንም አንስተዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሰላም ሀገር እየኖሩ እኛ በሰላም እንዳንኖር ጽንፈኛውን እየደገፉ መከራችን እያበዙት ነው፤ ሊበቃቸው ይገባል ነው ያሉት።

ሁሉም ልጆቹን መምከር፣ ግጭትን ማውገዝ እና ሰላምን መጠበቅ አለበትም ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚመለሱት በአንድነት፣ በኅብረ ብሔራዊነት እና በኢትዮጵያ ጥላ ሥር መኾኑን ገልጸዋል።

ከሀገር መከለካያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በመኾን አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ከችግር ለመውጣት በጉያችን ያለውን ማውጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ሕዝብ የክፉ ቀን መሪዎችን መጠበቅ እና ማገዝ እንደሚገባውም አንስተዋል። በአንድነት ካልተነሳን እየተዋረድን በየተራ እናልቃለን ነው ያሉት።

መንግሥትም ሕዝብን እያማረሩ የሚገኙ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን፣ ሙስናን እና ሌሎች ብልሹ አሠራሮችን ማስተካከል አለበት ብለዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በጦርነት ለማሳካት በተነሱ ኃይሎች ያጣናውን ሰላም በውይይት እና በምክክር መመለስ አለብን ብለዋል።

መራዊ እና ሜጫ በምርታማነቱ የሚታወቅ መኾኑን ያነሱት አሥተዳዳሪው ሜጫ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ሃብት የታደለ ቢኾንም በጽንፈኝነት በተነሱ ኃይሎች ከፍተኛ ዋጋ የከፈለ መኾኑን ገልጸዋል።

በሜጫ ምድር ንጹሐን ተገድለዋል፤ አሰቃቂ ድርጊት ተፈጽሟል፤ ንብረት ወድሟል፤ በዜጎች ላይ ከፍተኛ እንግልት ደርሷል ነው ያሉት።

ሜጫ እና አካባቢው የግጭት መጠንሰሻ ኾኖ መቆየቱን እና አሰቃቂ ግፍ የተፈጸመበት መኾኑንም አንስተዋል።

የእናቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የመምህራን የግፍ አገዳደል በቁጭት ሊያስነሳችሁ ይገባል ነው ያሉት።

ሰላም ከሌለ የሕዝብ እድገት ይቋረጣል፣ የትኛውም ጥያቄ ምላሽ አያገኝም ብለዋል።

ምክክር ሀገርን ያሳድጋል፤ ሰላምን ያረጋግጣል ብለዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በአንድነት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

በመንግሥት ቤት ኾነው ሕዝብን የሚያማርሩ አካላትን ከሕዝብ ጋር ኾነው እንደሚያጠሩም ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ ጽንፈኛው ቡድን ኩሩውን ሕዝብ ያጎሳቆለ እና አንገቱን ያስደፋ ነው ብለዋል።

የሀገር መከለካያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል መስዋዕትነት ባይከፍል ኖሮ አደጋው የከፋ ይኾን እንደነበርም አንስተዋል።

ጽንፈኛው ቡድን የኢትዮጵያን ክብር ለማዋረድ የሚሠራ ተላላኪ ቡድን መኾኑንም ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሕዝብ ሰላም የቆመ የሀገር ክብር ነው ያሉት አዛዡ ጽንፈኛው ግን በሀገር መከታው ላይ ክህደት ፈጽሟል ነው ያሉት።

የመኖር መብት እንዳይኖራችሁ ያደረጋችሁን፣ ምላስ የሚቆርጥን፣ እናት የሚገድልን፣ መስቀል የጨበጠ ቄስን አዋርዶ በጭካኔ የሚገድልን ቡድን ካልታገላችሁ ሰላም አታመጡም ነው ያሉት።

ቡድኑ የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ፣ ባንዳ እና ሀገር አፍራሽ መኾኑን ተናግረዋል። በሰላም እንዲገቡ ምከሩ፣ ገስጹ እምቢ ያለውን ግን አሳልፋችሁ ስጡ ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የሰላም ባሕል ከሌለ ዘላቂ ሰላምን እና ብልጽግናን ማረጋገጥ አይቻልም ብለዋል።

የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ታማኝነት፣ ታጋሽነት፣ ውይይት እና ምክክር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ምንጊዜም ለመመካከር፣ ለመደማመጥ እና ለመከባበር ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

በውይይቱ የግፉ ወላፈን እንደገረፋችሁ እና ግፍን ለማውገዝ መነሳታችሁን የሚያሳይ ምልክት አይተናል ነው ያሉት።

አሁን ያላችሁን ተነሳሽነት ተግባራዊ አድርጋችሁ ሰላምን ማረጋገጥ አለባችሁ ብለዋል።

ግፍን ለማውገዝ ሰው መኾን በቂ መኾኑንም ተናግረዋል።

ከሰከነ ሕዝብ ችግሮችን በውይይት እና በምክክር መፍታት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። አስተውሎት እና ስክነት ካለ ችግሮች ይፈታሉ፣ ብጥብጥ እና ሁከት አይኖርም ነው ያሉት።

ጽንፈኛው ቡድን ከአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር አማራን የሚያጎሳቁል መኾኑንም ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች ስለ እውነት ብለው ስለ ሰላም እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

ታጣቂ ቡድኑ በአስተሳሰቡ ጽንፈኛ፣ ተልዕኮው የጠላትን ፍላጎት የሚያስፈጽም፣ ድርጊቱ መዝረፍ እና ውንብድና ነው ብለዋል።

ጽንፈኛን እና ዘራፊ ቡድንን መደገፍ እና ማወደስ እንደማይገባም አስገንዝበዋል።

መንግሥት ችግሮችን ለመፍታት ሰላማዊ አማራጮችን አስቀድሞ መሥራቱንም ተናግረዋል።

አሁንም ለውይይት በራችን ክፍት ነው፤ ለውይይት የተዘጋጀ ካለ በፈለገው ጊዜ እና ቦታ ለውይይት ዝግጁ ነን ብለዋል።

የሰላም አማራጭን በማይቀበሉት ላይ ግን የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

እስካሁን በተሠራው የሕግ ማስከበር ተግባር የጽንፈኛው ቡድን ሕልም ቅዠት ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ለዘላቂ ሰላም የውይይት ባሕልን ማሳደግ፣ ግጭት እና ሁከትን አንጋሽ አለመኾን ይገባል ነው ያሉት።

“ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ግፍን ማውገዝ፣ ሐቅን መናገር እና ታማኝ መኾን ይጠበቃል” ብለዋል።

የአካባቢው መሪዎች የጸጥታ ኃይልን በማጠናከር ሰላምን እንዲያረጋግጥ ማድረግ እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። መካሪ እና ዘካሪ የሀገር ሽማግሌዎችን መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባም ገልጸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top