(ታሕሳስ 13/2018 ዓ.ም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ በእንጅባራ ከተማ ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ዓላማ የሌለው ነው ብለዋል። ታጥቆ ጫካ የገባው ኃይል ሕዝብ ሰላም፣ ሕይወት እና ምጣኔ ሃብት እንዲያጣ ማድረጉን ተናግረዋል።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ላደረገው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ክብርና ምስጋና ይገባዋል ነው ያሉት።
የታጠቀው ኃይል የአማራ ክልል በትምህርት፣ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ እንዳይኾን የሚሠራ አክሳሪ ቡድን መኾኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ በላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ጫካ ውሰጥ የሚገኘው ቡድን ላይ አስተማማኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አመላክተዋል። ሰላም በመንግሥት ኃይል ብቻ አይረጋገጥም፣ ለሰላም ሁላችንም መነሳት እና አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የሰላም ችግር በጋራ መፍታት እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ግጭት ሕዝብን ያጎሳቁላል፣ አንድነትን ይሸረሽራል፤ አብሮነትን ያጠፋል እንጂ ጥቅም የለውም ነው ያሉት።
ከሁሉም አስቀድሞ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ ሰላም ሲረጋገጥ የልማት ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል።
በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችን እየመከሩ እየመለሱ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ሰላምን በማይመርጡት ላይ ግን የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፤ እኛም እናግዛለን ነው ያሉት።
ሰላምን ከሁሉ ነገር አስቀድሙ፤ ሰላም ሲረጋገጥ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ እንፈልጋለን ብለዋል።
መንግሥት ከታጣቂዎች የጀመራቸውን የዘላቂ ሰላም ውይይቶች እና ስምምነቶች አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የችግር መድኃኒት ያለው ከውይይት መኾኑንም ገልጸዋል። ግጭት እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላትን ማረም እና ማስተካከል እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የልማት ጥያቄዎችን ከሌላ አጀንዳ ጋር ማያያዝ እና መንግሥትን ከሕዝብ ጋር ለመነጠል የሚደረጉ አካሄዶች መታረም እንዳለባቸው አሳስበዋል። የክልሉ መንግሥት በፍትሐዊ መንገድ የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የቆዬውን አብሮነት፣ ሰላም እና አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል። አብሮነትን ለመሸርሸር የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
የአዊ ብሔረሰብ ሕዝብ አብሮነትን፣ ሰላምን እና አንድነትን ይዞ የኖረ ነው፤ መገለጫውም ይሄው ነው፤ በዚህም መቀጠል አለበት ነው ያሉት። ሕዝብን ያማረሩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ ለጽንፈኛው ቡድን ባሳያችሁት የመረረ ጥላቻ ሰላምን ለማስከበር አግዛችሁናል ብለዋል።
ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በመቆም ለሰላም መስዋዕትነት መክፈላቸውንም ተናግረዋል።
የሀገር መከለካያ ሠራዊት ሀገር ጠባቂ የመጨረሻ ምሽግ ነው ያሉት አዛዡ ይሄን በመረዳት የሀገር መከለካያ ሠራዊትን በብዙ አግዛችኋል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባችኋል ነው ያሉት።
ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
በሕዝብ ስም እየነገዱ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሠሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
ታጣቂ ቡድኑ ንጹሐንን በግፍ የሚገድል፣ ንብረት የሚያወድም፣ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሁልጊዜው ሁሉ እንዲደግፉም አስገንዝበዋል። ጠንካራ ሀገር ለማስቀጠል ጠንካራ አንድነት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) አዊ ብሔረሰብ ለልማት ቆራጥ እና ጠንካራ ሕዝብ የሚኖርበት ነው ብለዋል። ባሕሉን እና ማንነቱን የሚጠብቅ፣ አብሮነትን የሚያጠናክር ሕዝብ ያለበት መኾኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ አካባቢያችሁን የጠበቃችሁ ምሳሌ እና አርዓያ የምትኾኑ ናችሁ ነው ያሉት።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝብን ለከፋ ጉዳት ዳርጓል ያሉት አሥተባባሪው ግጭቱን ከዕለታዊ ግጭት ባሻገር ማየት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በተላላኪዎች እና በባንዳዎች አማካኝነት ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትኾን እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ያለው ግጭት የውክልና መኾኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እድገት የሚያሰጋቸው ጠላቶች ክፍተቶችን በመጠቀም ግጭት እንዲባባስ እንደሚሠሩም አንስተዋል።
የመንግሥት የዘወትር ፍላጎት እና ጥረት ሰላም በማረጋገጥ ሕዝብ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን፣ ተማሪዎች እንዲማሩ፣ ነጋዴዎች እንዲነግዱ ማድረግ ነው ብለዋል። ታጣቁ ቡድኑ ግን ተማሪዎች እንዳይማሩ፣ ልማት እንዳይለማ፣ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር የሚያደርግ መኾኑን ተናግረዋል።
የሕዝብን ጥያቄ አስመልሳለሁ በሚል ማደናገሪያ የተነሳው ቡድን በሕዝብ ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰ መኾኑን ገልጸዋል።
ይህን ታጣቂ ቡድን በግልጽ ማውገዝ እና መታገል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ግፊት ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የአገው ሕዝብ የመቻቻል፣ የአብሮነት፣ የኅብረ ብሔራዊነት እና የአንድነት ተምሳሌት ነው ብለዋል።
የአገው ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ነጻነት እና ሰላም ዋጋ የከፈለ ኩሩ ሕዝብ መኾኑንም አመላክተዋል።
የአገው ሕዝብ የዳበረ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ እሴት፣ ታሪክ እና ወግ ያለው መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህ ሕዝብ ወጥቶ ሕዝብን ለማጋጨት የሚሠራው ጽንፈኛ ቡድን ለሕዝብ እንደማይጠቅም ተናግረዋል።
የአገው ሕዝብ የሚታወቀው በነጠላ ትርክት ሳይኾን በአንድነት፣ በኅብረ ብሔራዊነት መኾኑን ገልጸዋል።
የአገው ሕዝብ ጽንፈኛውን አልፈልግም በማለቱ ከሌሎች አካባባቢዎች በተሻለ መልኩ ሰላሙን ጠብቋል ነው ያሉት።
ይሄን ሰላም መጠበቅ እና ዘላቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችም በአንድነት ሰላማቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ነው ያሉት።
የታጣቂ ቡድኑ ፍላጎት ሥልጣንን በኃይል መያዝ ነበር፤ ነገር ግን ይህ አልሳካለትም፤ አይሳካለትም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ገናና እንድትኾን የማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች ቡድኑን እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
ጽንፈኛው የባዕዳንን ፍላጎት ለማሳከት እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማሳጣት እንደሚሠራም አንስተዋል።
መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሉንም የሰላም አማራጮችን መጠቀሙንም ተናግረዋል።
በተፈጠረው የሰላም አማራጭ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መጠቀማቸውን ገልጸዋል። ከሰላም አማራጭ ጎን ለጎን የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሕጋዊ ትግሎችን ማጠናከር እና ታጣቂ ቡድኑን መታገል እንደሚገባ ተናግረዋል። መሪዎች ሰርጎ ገብነትን መከላከል እና ሕዝብ ለሰላም እንዲነሳ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
የአገው ሕዝብ በቆዬው ታሪኩ፣ ባሕሉ እና እሴቱ ልክ ሢሠራ ዘላቂ ሰላሙን በአጭር ጊዜ ያጠናክራል ነው ያሉት።
የተነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።

