የአምራች ኢንዱስትሪዎችን እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉሉ ችግሮችን ክልሉ ኀላፊነት ወስዶ ይሠራል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

(ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም) የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል። ከጉብኝት በኋላም ከአልሚ ባለሃብቶች ጋር ውይይት አድርገዋል።

አልሚ ባለሃብቶች ቢፈቱ ያሏቸውን ጥያቄዎች አንስተዋል።

የገበያ ትስስር፣ የብድር አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የመንገድ፣ የመብራት እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮ ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “የአምራች ኢንዱስትሪዎችን እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉሉ ችግሮችን ክልሉ ኀላፊነት ወስዶ ይሠራል ብለዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የገበያ ችግር ለመፍታት ክልሉ ትኩረት እንደሚሰጠውም ገልጸዋል። ከገበያ ትስስር ውጭ የሚነሱ ችግሮችን በአሠራሩ መሠረት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት ይሠራል ነው ያሉት።

የክልሉ ካውንስል ኮሚቴም በወረዳዎቹ እና ከተሞች የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ተከታትሎ በራስ አቅም የሚፈቱ ችግሮች እንዲፈቱ ይደረጋል ብለዋል።

በውይይቱ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ኢንዱስትሪዎች ከአርሶ አደሮች ጋር ያላቸው ትስስር፣ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን በመጠን እና በአይነት የማምረት አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ከብድር ጋር ለተነሳውን ጥያቄ በባንኮች በኩል ክፍተት የመኖሩን ያህል በባለሃብቶች በኩልም ለብድር አገልግሎት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን የማቅረብ ችግር እንዳለ አንስተዋል።

የመሠረተ ልማት፣ የገበያ ትስስር እና ሌሎች በአምራች ኢንዱስትሪዎች የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የሚሠራ ይኾናል ብለዋል።

የፌዴራል አምራች ኢንዱስትሪ ካውንስሉ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር ለመፍታት የተቋቋመ መኾኑን ያነሱት ሚኒስትሩ የክልሉ ካውንስል ኮሚቴም በወረዳዎቹ እና ከተሞች የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን በመከታተል በክልሉ አቅም የሚፈቱ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ ደግሞ ካውንስሉ የተነሱ ጥያቄዎችን ከሚመለከታቸው ተቋማት አሠራር አኳያ ምላሽ እንዲያገኙ ይሠራል ብለዋል።

ባንኮች ባላቸው የብድር ፖሊሲ ለአልሚ ባለሃብቶች የሚያቀርቡበትን አሠራር፤ አልሚዎች ደግሞ ብድር ለማግኘት የሚያበቃቸውን መስፈርት አሟልተው መቅረባቸውን ክትትል ያደርጋል ነው ያሉት።

ሌሎች ተቋማትም አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያነሷቸውን ችግሮች በአሠራሩ መሠረት በፍጥነት እንዲፈቱ ካውንስሉ እንደሚሠራ አንስተዋል።

ከአሠራሩ ውጭ ኾኖ በተገኙት ላይ ደግሞ እርምጃ እንደሚወሰድ ነው የገለጹት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top