“ከችግር መውጫ መንገዱ እውነት ላይ መቆም ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

(ታሕሳስ 8/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከቡሬ ከተማ እና ከቡሬ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ቡሬ የኅብርነት ምልክት ናት፤ የቀጣይ የአማራ የኢንዱስትሪ ማዕከልነት መፈልፈያ እና ተስፋ ናት ብለዋል።

ይህ ቦታ በጸጋው እንዲጠቀም እንጂ ለጽንፈኝነት ሃሳብ መንሸራሸሪያ እንዲኮን መፍቀድ አይገባም ብለዋል።

ሃሳባችሁም የቡሬን ኅብራዊነት ምልክት እና የኢንዱስትሪ ማዕከልነት የሚመጥን መኾን አለበት ብለዋል። ሰላም እንዲረጋገጥ እውነት ላይ ቆሞ መወያየት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኅብረብሔራዊነት ባለባት ቡሬ ውስጥ ጠላት ብዙ ሴራ ሊሠራ እንደሚችል መረዳት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የጽንፈኛው ቡድን መነሻ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ መኾኑን ገልጸዋል። ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመኾን ኢትዮጵያን ለማሳነስ፣ ለማፍረስ እና ጠንካራ መንግሥት እንዳይኖር እንደሚሠራም ተናግረዋል። ጽንፈኛው ቡድን የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ እና ባንዳ መኾኑንም ገልጸዋል።

የጽንኛው ቡድን አሰላለፍ ከጠላት ጋር ግብሩ ደግሞ መዝረፍ እና መቀማት ነው ብለዋል።

ከችግር መውጫ መንገዱ እውነት እና ሀቅ ላይ መቆም ነው፤ ሰላም፣ ሽምግልና እና እርቅ የሚፈልገው እውነት ስለኾነ እውነት ላይ ቁሙ ነው ያሉት።

የአካባቢው መሪዎች የአካባቢውን የጸጥታ ኃይል ማጠናከር፣ ሰላምን ማረጋገጥ እና ጽንፈኛውን እያሰሰ እንዲያጸዳ ማድረግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል። ቡሬ ያለውን ጸጋ እንዲጠቀም ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲመክሩ፣ እንዲገስጹ እና ሰላምን እንዲያረጋግጡም ጠይቀዋል።

በሕዝብ ዘንድ የተነሱ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ እንደሚሠራም አመላክተዋል።

የአካባቢው መሪዎች የመልካም አሥተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን እንዲፈቱም አሳስበዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top