(ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በፍኖተ ሰላም ከተማ እየተገነቡ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቹ የፍኖተ ሰላም ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት እና ሞዴል ትምህርት ቤትን ነው የጎበኙት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ የስጋት ደሴ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት በመገንባት በኩል ክፍተት እንደነበር ተናግረዋል።
አሁን ላይ ግን ታላላቅ የትምህርት ተቋማት እየተገነቡ ነው ብለዋል።
በክልሉ መንግሥት እና በፌዴራል መንግሥት እየተገነቡ የሚገኙት ተቋማቱ የነገዋን ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ የሚወስኑ ልጆች የሚፈልቁባቸው ናቸው ነው ያሉት።
የፍኖተ ሰላም ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እየተገነባ መኾኑንም ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ በ2019 ዓ.ም ወደ አገልግሎት እንዲገባ ታሳቢ በማድረግ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
ለአካባቢው ማኅበረሰብ ትልቅ ተስፋ የሰጠ መኾኑን ተናግረዋል። የዘገዩ ሥራዎችን ማፋጠን እንደሚገባም አንስተዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የሚገነባው ሞዴል ትምህርት ቤት በ506 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተያዘለት ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱ በፍጥነት እየተገነባ መኾኑንም ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቶቹ በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የተጠናከረ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግ አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ጥራት ያለቸው የትምህርት ተቋማትን መገንባት እና ተቋማቱን በግብዓት ማሟላት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ጥራት ላላቸው ተቋማት ትኩረት በመስጠት ልዩ አዳሪ ትምህ ቤቶችን እያስገነባ መኾኑን ተናግረዋል።
የፍኖተ ሰላም፣ የደብረ ታቦር እና የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በግንባታ ላይ መኾናቸውን አንስተዋል።
በክልሉ መንግሥት እየተገነባ የሚገኘው የፍኖተ ሰላም ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት እና በትምህርት ሚኒስቴር እየተገነባ የሚገኘው ሞዴል ትምህርት ቤት የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የፍኖተ ሰላም ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በሁለት ተቋራጮች እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አንደኛው ተቋራጭ ዘግይቷል፤ የዘገየበትን ምክንያት በመገምገም ማስተካከያ ይደረግበታል ነው ያሉት።
በትምህርት ሚኒስቴር እየተገነባ የሚገኘው ሞዴል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ በተያዘለት ጊዜ መሠረት እየሄደ መኾኑን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶቹ በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ጥሩ ውጤት እያመጡ መኾናቸውን የተናገሩት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እየሰፉ እንዲሄዱ የግል ባለሀብቶች፣ መንግሥት እና ሕዝብ በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። ቅንጅታዊ አሠራር እንዲኖር ይሠራልም ብለዋል።
የልማት ድርጅቶች እና ባለሀብቶችም በዘርፉ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ላይ ከመሥራት ባሻገር የሌሎች ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የተሻለ ተማሪዎች እንዲወጡ የቅድመ መደበኛ እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚሠራው ሥራ ታላቅ መኾኑንም ገልጸዋል።

