“ሰላምን ለማረጋገጥ እውነት ላይ የተመሠረተ ምክክር ያስፈልጋል” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

(ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ ጎጃም ዞን ከደምበጫ ከተማ አሥተዳደር እና ከደምበጫ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ ረጋሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ የጸጥታ ችግሩ በደምበጫ አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

ነጋዴዎች መሰደዳቸውን፣ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ መራቃቸውን፣ የልማት ሥራዎች መቋረጣቸውን እና ሕዝቡ በስነ ልቦና ጫና መቆየቱን ነው የተናገሩት።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ ኀይል አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩንም ገልጸዋል።

ደምበጫ እና አካባቢው ለግብርና ልማት የተመቸ፣ የማዕድን ሃብት ያለው ባለጸጋ ነው ብለዋል።

በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ግን ሕዝቡ ያለውን ሃብት እንዳይጠቀም ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት።

አሁን ላይ የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ እንዲኾን መመካከር እና የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ለማጽናት በልዩነት መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ሰላም የሚጸናው ሕዝብ ሲታከልበት ነው ብለዋል። ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማድረግ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል። ሰላምን መጠበቅ፣ ሰላምን በጋራ ማጽናት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት የግጭት ቀማሽ ኾኖ ቆይቷል፤ የሰላም ትሩፋት አጥቶ ከርሟል ነው ያሉት።

በክልሉ ከደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በላይ የደረሰው የእሴት መሸርሸር ለነገ ዳፋው ፈተና ነው ብለዋል። ይህ ዳፋ እንዳይሰፋ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የሰብዓዊ ልማት ሥብራቱ ከፍ ያለ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ባለፉት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፤ ይህ ማለት ነገ ሕዝብ የሚያክም ሐኪም፣ የሚያስተምር መምህር፣ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ምሁራን አይኖርም ማለት ነው ብለዋል።

ይህን ችግር በፍጥነት መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል። የተፈጠረው የጸጥታ ችግር አንድነትን እንደሚሸረሽርም ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ በቀጣይ ለሚሠሩ ሥራዎች ፈተና ስለኾነ በአጭር ጊዜ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ሰላምን ለማረጋገጥ እውነት ላይ የተመሠረተ ምክክር ያስፈልጋል ነው ያሉት። እውነት ላይ የተመሠረተ ምክክር እና ንግግር ሰላምን ዘላቂ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ውይይቱ እውነት ላይ የተመሠረተ ካልኾነ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት እንደማይችል ነው የገለጹት ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top