“የሕዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ የግብርና ልማት ሥራን ማስፋት ይገባል”- አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር)

የተቀናጀ የግብርና ልማት ሥራ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቹ የምሥራቅ ጎጃም ዞን የአሥተዳደር ሕንጻ ግንባታ፣ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሕንጻ ግንባታ፣ የጎዛምን ወረዳ የተቀናጀ የግብርና እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል፣ የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት እና ሌሎች ሥራዎችን ነው የጎበኙት።

በጉብኝቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የጎዛምን ወረዳ አሥተዳዳሪ ዓለሙ ውበት በወረዳው የተቀናጀ የግብርና እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል በማቋቋም ዘመናዊ ግብርናን ለማስፋፋት እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በጓሮ አትክልት፣ በድሮ ርባታ፣ በዓሳ ሃብት ልማት፣ በወተት ልማት እና በእንስሳት ማድለብ በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል።

እየተሠሩ ባሉ የተቀናጁ የግብርና ልማት ሥራዎች ለመንግሥት ሠራተኞች በዝቅተኛ ዋጋ እያቀረቡ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ወተት፣ የጓሮ አትክልት እና እንቁላል በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚያቀርቡ ነው የገለጹት።

ማዕከሉ ለአርሶ አደሮች የተሞክሮ መቀመሪያ መኾኑንም አንስተዋል።

የተቀናጀ የግብርና ልማትን ማስፋፋት በትኩረት ይሠራበታል ነው ያሉት።

አርሶ አደሮች የኑሮ ደረጃቸውን እና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የሚያደርጉ ዕቅዶችን አቅደን እየሠራን ነው ብለዋል።

በወረዳው የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት ተግባራዊ ማድረግ መቻላቸውንም ተናግረዋል።

ሥልጡን መንደርን ለመገንባት በጀት መድበው እየሠሩ እንደኾነም ተናግረዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) የሕዝብን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት ከሚሠራባቸው ጉዳዮች መካከል ዘመናዊ ግብርና ነው ብለዋል።

በጎዛምን ወረዳ የተመለከቱት የተቀናጀ የግብርና ልማት አስደሳች መኾኑን ተናግረዋል። የታቀደው ዕቅድ መሬት ላይ እየተተገበረ መኾን አይተናል ነው ያሉት።

የተቀናጀ የግብርና ልማት ሥራ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና በሁሉም አካባቢዎች መስፋፋት የሚገባው ነው ብለዋል።

ሃብትን በተገቢው መጠቀም ከተቻለ የኑሮ ውድነትን ማስተካከል የሚያስችል እና ተሞክሮ መኾን የሚችል ሥራ መሥራት ይቻላል ነው ያሉት።

በዞኑ እየተገነቡ የቢሮ ግንባታዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾኑ እንደሚሠራም አመላክተዋል።

ግንባታቸውን በማጠናቀቅ ለሥራ የተመቹ ከባቢዎችን ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top