(ኅዳር 29/2018 ዓ.ም) 20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ‘’ዴሞክራሲያዊ መግባባት፣ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ መልዕክት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መናገሻ በኾነችው ሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ነው።
በፕሮግራሙ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸው በጀግንነቱ፣ በሀገር ወዳድነቱ እና በአቃፊነቱ የሚታወቀው የሀድያ ብሔረሰብ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ተሰባስበን በዓላችንን እንድናከብር ስላደረጋችሁ እናመሰግናለን ብለዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስንሰባሰብ ብሔራዊ እንድነትን በመሻት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በኅብር ቀለም የሚሳል፣ በኅብር ባሕል የሚኖር፣ በኅብር ቋንቋ የሚነገር፣ በኅብር ደም የተሠራ፣ በኅብር ላይ የሚገነባ፣ በኅብር ጥበብ የሚሻገር እሳቤ በመኾኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውይነት የነበሩ፣ የሚኖሩ እና የሚጸኑ መኾናቸውንም አስረድተዋል። የአንዱ ባሕል ለሌላው ኩራቱ፣ ሀብቱ፣ ሀሴቱ፣ ታሪኩ እና ቅርሱ እንኾነም ገልጸዋል።
በመደመር እሳቤ ከፍ እና ዝቅ ብለን ሳይኾን በእኩልነት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማሻገር እንደሚገባ አደራ ብለዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ኅብረ ብሔራዊነትን እያጠናከርን፣ በገዥ ትርክት እየተሸመን፣ በተቋማዊ ለውጥ የሀገር ግንባታ እና የሀገረ መንግሥት ማጽናት ጅማሯችንን እያጎለበትን የጸናች ሀገር ለልጆቻችን ልናስረክብ ይገባልም ሲሉ አክለዋል።
ስንተባበር ጠንካራ እንኾናለን፤ በመተባበር ብሔራዊ ጥቅማችንን ልናስቀድም እና ልናስጠብቅ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ተስፋዎች አሏት። ተስፋዋን ለማደናቀፍ የተፈጠሩ ፈተናዎችን በትጋት እናልፋለን ነው ያሉት።

