‘ከጂኦ ስትራቴጂካዊ ኩስምና ወደ ታደሰ ቁመና’ በሚል መሪ ሀሳብ ለአማራ ክልል ፖሊስ ስትራቴጅክ እና ከፍተኛ አመራሮች በተሰጠው የጂኦ ስትራቴጂካዊ ስልጠና ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ሀገራችን የጀመረችው ብሄራዊ ጥያቄ የመብትና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይልና ህዝብ በባለቤትነት በመቀበል እና በተሰማራበት የስራ ዘርፍ ስኬታማ በመሆን ሀገራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ የአማራ ክልል ፖሊስ የክልሉን ብሎም የሀገራችንን ብሄራዊ ጥቅምና ሰላምን የሚያውኩ ባንዳዎችንና ተላላኪዎችን በማጽዳት በኩል ማህበረሰቡን ያሳተፈ የህግ ማስከበር ስራ ሰርቷል ብለዋል።
በመንግስት በኩል በአጀንዳ ተይዘው በሂደት መልስ የሚጠብቁ በአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ስም ሀገርንና ህዝብን የሚያውኩ አካላት ወደ ሰላማዊ መንገድ እስካልተመለሱ ድረስ የሚደረገው ህግ የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በብሄራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጉዳይ የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይል ባለቤት በመሆን ታሪካዊ አርበኝነቱን የሚያረጋግጥ ሰራዊት መገንባት ያስፈልጋል ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበርና ሀገራዊ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ሲባል ለመስዕዋትነት የማያመነታ የጸጥታ ኃይል እና በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የማይደራደር ህዝብ ያላት ሀገር ለመሆኗ በዓለም አደባባይ የተመሰከረላት ናት ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አብራርተዋል።
ሀገሪቱ የጀመረችው የባህር በር ጥያቄ ሀገራዊ የህልውናና የመብት ጥያቄ በመሆኑ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብና አድወዋ ድል ዳግም የመቻል አቅማችንን የምናሳይበት መሆኑን ነው የገለጹት።
የፖሊስ ሰራዊቱ የሚወዳት ሀገር፣ የሚያገለግለው ህዝብ እንዲሁም የሚያስከብረው ብሔራዊ ጥቅም አለው ያሉት ኮሚሽነሩ ይሄን ለማሳካት ጽናትን፣ ትጋትን፣ አርበኝነትን እና አገልጋይነት መላበስ ያሻል ብለዋል።
“የህዝብ አገልጋይነት መገለጫው መስዋዕትነት ነው” ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ የፖሊስ አመራር በተሰማራበት ቦታ ሁሉ በአርበኝነት እና በትጋት በመስራት የአመራርነት ቁልፍ ሚናውን መወጣት ይጠበቅበታል።
ለጠላት ጥቃት ምቹ ሁኔታን ከሚፈጥሩ ድርጊቶች በመቆጠብ እና ክፍተቶችን በመዝጋት ህዝባዊ እና ብሔራዊ ለሆነው አላማችን በጽናት መቆም ይገባል ሲሉ አክለዋል።
የቆምንለትን አላማ ለማደናቀፍ ቀን ከሌት ከሚታትሩ ባንዳዎችና ሰርጎ ገቦች በመራቅ የህዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ በትጋት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኝ የፖሊስ አመራር የአካባቢውን ሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም ሁለንተናዊ ጉዳዮችን በንቃት መከታተል እና ስራውን በጥንቃቄና በትኩረት መምራት ይገባዋል ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በጂኦ ስትራቴጂካዊ ስልጠናው ለተሳተፉ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ብርሃኔ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሀብት ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው የአማራ ክልል ፖሊስ ከሌሎች የፌደራል እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ እያደረገ ባለው ተጋድሎ የህዝብን ሰላምና ልማት የሚያውኩ ቡድኖች እና የተላላኪ ባንዳዎችን ሴራ ማክሸፍ ችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል ከዘመኑ ጋር የዘመና በስነልቦና የተገነባ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ብርሃኔ ይህም ለጅኦ ፖለቲካ ምህዳሩ እና ለሀገራችን የሉዓላዊነት መረጋገጥ ትልቁ ማሳያ ምልክታችን ነው ብለዋል።

