ግባችን የህዝብ እርካታን ማረጋገጥ ነው- ክቡር አረጋ ከበደ

(ሕዳር 6፣ 2018 ዓ.ም) የመጨረሻ ግባችን የህዝብ እርካታን ማረጋገጥ ነው አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አረጋ ከበደ፤

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከርዕሰ መስተዳድሩ ጋር በመሆን የደሴ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው አስጀምረዋል።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን ለመቅረፍ ወሳኝ ሚና አለው።

በክልሉ በሦስት ከተሞች ማለትም በባሕር ዳር፣ ጎንደርና ደሴ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩን ገልጸው÷ በቅርቡም በደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ወልድያ፣ ደብረ ታቦር እና ደብረ ማርቆስ የመሶብ ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቁመዋል።

በመሶብ የአገልግሎት ማዕከላት የህዝቡን እርካታ በሚያሳድግና ልማትን በሚያፋጥን መልኩ አገልግሎት መስጠት ይገባልም ነው ያሉት።

የደሴ ከተማ ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው÷ ከተማ አስተዳደሩ ከህዝብና ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር በርካታ የልማት ሥራዎች ማከናወኑን ጠቅሰዋል።

የመንገድ መሠረተ ልማት፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማት፣ የኑሮ ውደድነትን የሚያረጋጉ የገበያ ማዕከላትን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አንስተዋል።

ከተማዋ ከለውጡ በፊት ከልማት ወደ ኋላ የቀረች መሆኗን በማውሳት÷ ከለውጡ ወዲህ ፈጠራ መርህ የፕሮጀክት ትግበራን በመከተል በርካታ የልማትና የአገልግሎት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

ዛሬ የተመረቀው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትም በሁለት ወራት ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱን አንስተው÷ ይህም በራስ አቅም እቅድን በፍጥነት የማሳካት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top