የባሕር ዳር ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ባለፉት አራት ወራት ከ337 ሚሊየን 362 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣውን ተኪ ምርት ለገበያ አቀረበ።
የልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ጥሩየ ቁሜ እንዳሉት ዞኑ ተኪ ምርቶችን በማምረትና ወደ ገበያ በማቅረብ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ጫናን ለመቀነስ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም ትራንስፎርመር ማምረት፣ አኩሪ አተር ዘይት እንዲሁም ከቦቆሎ ስታርች በማምረትና ለሀገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ከተሰማሩ አምስት ባለሃብቶች ሦስቱ የተሻለ አፈፃፀም እያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው ሁለቱ በተሟላ ሁኔታ ወደ ስራ አለመግባታቸውን አመላክተዋል።
የልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ በፓርኩ ውስጥ ባሉ ድርጅቶችና የሀገር ውስጥ አምራቾች መካከል ያለውን ትስስር የማጠናከር ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም ባለፉት አራት ወራት 332 ሚሊየን 466 ሺህ 110 ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩን አመላክተዋል።
በዞኑ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ኢንዲሰማሩ ለማስቻል የተለያዩ የማሻሻያ ውሳኔዎች መደረጋቸውን አንስተው÷ በዚህም የለማ መሬት ሊዝ ዋጋ ላይ በፊት ከነበረው 8 ነጥብ 1 ዶላር ወደ 2 ነጥብ 6 ዶላር ዝቅ መደረጉን ተናግረዋል።
እንዲሁም የክፍያ ጊዜው 10 ዓመት የነበረው ወደ 40 ዓመት ከፍ መደረጉን፣ የቅድመ ክፍያ 5 በመቶ በ1 ጊዜ የነበረው በ2 ጊዜ መክፈል እንዲቻል፣ የእፎይታ ጊዜ 1 ዓመት የነበረው አሁን 2 ዓመት ተደርጓልም ነው ያሉት።
በተጨማሪም የሼድ ኪራይ ክፍያ በካሬ 2 ዶላር የነበረው ወደ 1 ነጥብ 5 ዶላር ዝቅ፣ የእፎይታ ጊዜ ከ3 ወር ወደ 4 ወር ከፍ እና የቅድመ ክፍያ 3 ወር የነበረው ወደ 1 ወር ዝቅ መደረጋቸውን አስረድተዋል።

