የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዘላቂ ሰላም በጋራ መሥራት ይገባቸዋል።

(ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ውይይት እየተካሄደ ነው።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማሥተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በውይይቱ ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ የክልሉ መንግሥት ለጋራ ሀገራችን የጋራ ውይይት እንድናደርግ መድረኩን በማዘጋጀቱ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደኾነም ተናግረዋል። በሀገር ደረጃ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እውን እንዲኾን እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

በፓርቲዎች መካከል በመከባበር ላይ የተመሠረተ ጤማ ግንኙነት እንዲኖር እየተሠራ እንደኾነም ነው የተናገሩት። ችግሮች በውይይት እንዲፈቱም በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መንግሥት በኢትዮጵያ የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመፍጠር እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የፖለቲካ ምህዳሩን የተመቸ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

የዴሞክራሲ ልምምድን ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ሁነኛ እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚሠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ሲመዘገቡ የሕዝብን ሰላም መጠበቅ እና የሀገሪቱን ሕጎች ማክበር እንዳለባቸው እንደሚደነግግ አንስተዋል።

በአማራ ክልል ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ የተነሱ ኃይሎች በክልሉ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሳቸውንም ገልጸዋል።

ይህ አካሄድ ደግሞ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት እና የፖለቲካ መህዳሩን ለማስፋት አይመችም ነው ያሉት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዘላቂ ሰላም መሥራት እንደሚገባቸው እና የሀገሪቱን ሕጎች ማክበር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እየተገናኙ መወያየት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የሀገርን ልማት ለማረጋገጥ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ይገባል ነው ያሉት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርስ የሚኖራቸው ግንኙነት አርዓያ የሚኾን እና ለሀገር ሰላም መረጋገጥ በጋራ የሚሠራ መኾን ይኖርበታል ነው ያሉት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top