(መስከረም 28/2018 ዓ.ም) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
አቶ አደም ፋራህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መዲና በሆነቸው በውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ በመገኘት ከክልሉ መሪዎች ጋር በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸሻለ የሚገኘው የክልሉ የሰላም ሁኔታ በዘላቂነት መሠረት እዲኖረው መሪዎች ከኅብረተሰቡ ገር እጅና ጓንት ኾነው የፓርቲ እና የመንግሥት አቅጣጫዎችን ተግባራዊ እያደረጉ የሚገኙበት ርቀት ይበል የሚያሰኝ ኾኖ አግኝተነዋል ነው ያሉት።
በተመሳሳይም በልማት ሥራዎች ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ የእርሻ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የኮሪደር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና መሰል ሥራዎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እና የክልሉንና የሀገራችን ኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከመደገፍ አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል።
በተጨማሪም የፖለቲካ እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ጥራት፣ ተደራሽነት እና ብስለት ማዕከል በማድረግ መሠረታዊ ለውጥን በሚያመጣ መልኩ እየተከናወኑ መኾኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በአማራ ክልል በነበረን ቆይታ በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ሥራዎችን አቀናጅቶ በመምራት ሕዝቡን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት በማገልገል መኾናቸውን፤ መላው ኅብረተሰብ ከመንግሥት ጎን በመኾን በቅንጅት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ፍሬያማ መኾናቸውን ተመልክተናል ነው ያሉት።
በቀጣይም ኅብረተሰቡ በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል እንደ ብልጽግና ፓርቲ ያለን እምነት ጠንካራ መኾኑን እገልጻለሁ ብለዋል።
የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠልና እርማት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን መፍትሔ እየሰጡ ለመሄድ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ እላለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
