(መስከረም 25/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት እና የሕዝብን መሥተጋብር እንደሚያሻሽል ታስቦ ተቋቁሞ እየተሠራበት መኾኑን ተናግረዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መነሻው ሕዝቡ ከመንግሥት ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት በተገቢው መንገድ እንዲያገኝ ለማስቻል ነው ብለዋል።
ይህም መንግሥት አገልግሎቱን በጥራት ለመሥጠት የወሰደው ቁርጠኝነት መኾኑን ነው ያመላከቱት።
የአንድ ሞሰብ አገልግሎት ሕዝብ ሩቅ ሳይሄድ ከመንግሥት ማግኘት የሚጠበቅበትን አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ ለማስቻል ያለመ መኾኑንም ገልጸዋል።
አገልግሎቱ በተቋማት የሚስተዋለውን ብልሹ የአገልግሎት አሰጣጥ እንደሚያሻሽልም ገልጸዋል። ወጭን እና ጊዜን ቆጣቢ፣ ቀልጣፋ እና እርካታን የሚያረጋግጥ አሠራር መኾኑንም ነው የገለጹት።
አገልግሎቱ የዜጎችን ኑሮ ያሻሽላል፤ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ያሳልጣል፤ የማኀበረሰብን እና የሀገርን ዕድገት ለማረጋገጥ ያስችላል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።
በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ማኅበረሰቡ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት ማግኘቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
በአግባቡ አገልግሎት በማይሰጥ ተቋም፣ መሪ እና ባለሙያዎች ላይ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባም ገልጸዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት “ማገልገል ግዴታ አገልግሎት ማግኘት ደግሞ መብት መኾኑ የሚረጋገጥበት ነው” ብለዋል።
ማኀበረሰቡ መብቱን በገንዘብ መሸጥ እንደሌለበት እና መብቱን በመጠየቅ ለአገልግሎት አሰጣጡ አወንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በሁሉም የመንግሥት እርከን ያለው አሥተዳደር ሁሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባውም አሳስበዋል። በዚህ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችም የተጣለባቸውን ኀላፊነት መወጣት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
ለውጤታማነት ተቋም መገንባት ብቻ ሳይኾን በሰው አዕምሮ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ርእሰ መሥተዳደሩ አውቆ በሚያጠፋው ላይ ደግሞ ያለ ምህረት መታገል እና ማረም ይገባል ለዚህም ሕዝቡ ተባባሪ መኾን ይገበዋል ብለዋል።
በሁሉም ደረጃ የሚገኘው መሪ፣ የመንግሥት ሠራተኛ እና ባለሙያው ተገልጋዩ ሕዝብ የተቃና አገልግሎት እንዲያገኝ መትጋት እንደሚገባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
የሕዝብን እርካታ የሚያረጋግጥ፣ ሀገርን የሚያሳድግ የተሳለጠ አገልግሎት በመስጠት በትጋት መሥራት ከሁሉም መሪ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
የሞሰብ አንድ ማዕከል አገልግሎቱ በሚቀጥሉት ጊዜያት በጎንደር እና በደሴ ከተሞች እንደሚጀመርም አመላክተዋል። በቀጣይም በሌሎቹ ሪጆ ፖሊታንት ከተሞች እየተስፋፋ አንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
