በሰሜን ወሎ ዞን በመቄት ወረዳ እና ፍላቂት ገረገራ ከተማ አስተዳደር በጫካ የነበሩ ታጣቂዎች መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በሰላም መግባታቸው ተገለጸ።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች እንዳሉት፦ ከእንግዲህ ወጣትነታችን ለልማትና ለሰላም ግንባታ እንጂ ለጥፋት አናውለውም። የበደልነውን ሕዝብ በመካስ ሰላማዊ ህይወት ለመምራት ቆርጠን በመወሰናቸውን የሰላምን አማራጭ ተቀብለን በሰላም ገብተናል።
ሌሎች ሳይገባቸው ጫካ የወጡ ሀይሎችም የሰላምን መንገድ በመምረጥ መምጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በአቀባበሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የፍላቂት ገረገራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አንደበት ተስፋየ እና የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋጋው መንበር፦ ገብቷችሁም ይሁን ሳይገባችሁ ጫካ በመውጣት ትግል ስታደርጉ ቆይታችኋል።
ትግሉ ከኪሳራ ውጭ ትርፍ የለለው መሆኑን በመረዳትና ሰው ከስትት የሚማር ፍጡር በመሆኑ ከተሳሳተ አላማ ወጥታችሁ በሰላም እጅ ለመስጠት በመብቃታችሁ ታላቅ ምስጋና አለን ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርጫፍ ፅ/ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ወንድምነዉ ወዳጀ እና በሀገር መከላከያ ሰራዊት የ47ኛ ክፍለ ጦር የ4ኛ ሬጅመንት አዛዥ ሻንበል ሲሳይ ኤፍሬም በበኩላቸው፦ ተሰማርታችሁበት የነበረው ትግል ከእርስበርስ ግድያ ውጭ ትርፍ የለለው እና የአማራን ህልውና ከማስጠበቅ ይልቅ ክልሉን ወደኋላ እንዲመለስ የሚያደርግ ነው።
ይህ እኩይ አላማ ገብቷችሁ በሰላም በመምጣታችሁ ደስተኛ ነን ብለዋል። በቀጣይም የቀሩ ወንድሞቻችን በሰላም እንዲገቡ ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል መሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
በእለቱ የወረዳና የከተማ አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት፣ የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የአድማ መከላከል አመራሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት መገኘታቸውን ከመቄት ወረዳ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

