በአማራ ክልል የ2018 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋስስ ልማት ትግበራ ማሰጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ በከሚሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩም በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅ/ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍሰሃ ደሳለኝ፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ፣ የክልል፣ የዞን አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የተፈጥሮ መዛባት በመከላከል የማይበገር ግብርና ለመፍጠር የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ወሳኝ ነው ያሉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራችን ያለንን የመሬት ሀብት ተጠቅመን ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍ አሻራ የምናስቀምጥበት ነው ብለዋል።
በክልሉ ከ4.5 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበት ከ9ሺ በላይ ተፋሰሶች ላይ የአፈር እቀባ ስራ የሚሰራበት ትልቅ የህዝብ ንቅናቄ የሚፈጠርበት ሲሆን በክልሉ ባሉ ሁሉም አካባቢ በመተግበር በዚህ አመት ያስቀመጥነውን ግብ የምናሳካበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራችን የግብርና መዋቅራዊ ሽግግርን ለማሳካት አንዱ የርብርብ ማዕከል ነው ያሉት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የዛሬን ምርታማነት ከነገው ትውልድ ፍላጎት ጋር በማጣጣም ዘላቂ እድገትን የሚያረጋግጥ ዋና መሠረት ነው በማለት አሳስበዋል።
በዘንድሮ በጀት ዓመት 267,217 ሄክታር መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የሚሰራበት ሲሆን፣ 99,774 ሄክታር መሬት ከልሎ በማገገም እንዲሁም 189,235 ሄክታር የደረጃ የማሳደግ ስራ ይሰራል ብለዋል።
በተፋሰስ ደረጃ የሚከናወኑ የአፈር እና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች የማህበረሰብ ተሳትፎን በማጠናከር ባለቤትነትን የሚፈጥር ዘላቂነት የሚያረጋግጥ ተግባር መሆኑን ገልፆል።
የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ የ2018 የተፈጥሮ ሀብት ስራችን ባደገ መልኩ በመተግበር መሰረት በመጣል የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

