ከተሞች የማሕበረሰብ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ ትብብር እና አብሮነት ውጤቶች ናቸው። የማሕበረሰብ አንድነት ማስተሳሰሪያ ገመድ ናቸው።
ጠንካራ የጋራ ማሕበራዊ መስተጋብር የሚጸባረቀው በከተሞች ነው። ከተሞች አብሮ የመኖር መገለጫ፣ በጋራ ሰርቶ መለወጫ ማዕከላት ናቸው።
በአንድ ከተማ የሚኖረው ሕዝብ ለከተማው ሰላም፣ እድገትና መለወጥ በጋራ ይመክራል፤ በጋራ ይሰራል። ለጋራ ሰላምና ልማት በቅንጅት ይጥራል። በትብብር ስልጡን ከተማን ይገነባል። ይፈጥራል።
ከተማ ደግሞ ብዝሃ ዘርፍ የልማት እንቅስቃሴ የሚከናወንበት፣ የግብይት እና የንግድ ስርዓት የሚሳለጥበት፤ የኢኮኖሚ ሽግግር የሚፈጠርበት ነው። ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማጠንጠኛ ለእድገትና ብልጽግና መዳረሻም ነው።
በተጨማሪም የከተሞች እደገት ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ሁነኛ አቅም ነው። ከከተሞች እድገትና ስልጣኔ በተጨማሪ ለዘርፉ እድገት የተመቸ መልካም ባሕል እሴቶች አለን። ይሔን መልካም ጸጋ አስተሳስሮ ወደ እሴት ቀይሮ መጠቀም ይጠይቃል።
የክልላችን ከተሞች በተለያዩ ወቅትና ጊዜ በርካታ ባሕላዊ እና ኃይማኖታዊ ኩነቶች የሚከናወኑባቸው ናቸው። ይህ ደግሞ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ሁነኛ መደላድል ነው።
ለቱሪዝም ዘርፉ ውጤታማነት የከተሞች ሁለንተናዊ ለውጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል። በክልላችን የሚገኙ ከተሞችን በኮሪደር ልማት በማዘመን ለነዋሪዎች ምቱ፤ ለጎብኚዎች ተፈላጊ እንዲሆ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ እና በሌሎች ከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ዘመናዊ ገጽታ እንዲላበሱ አደርጓል። በውስን የክልላችን ከተሞች የተጀመረው ኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ በሌሎች ዞንና ወረዳ አስተዳድር ከተሞች እየተተገበረ ይገኛል።
ከተሞችን ምቹ፣ ሳቢ፣ ተስማሚና አረንጓዴ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ከተሞችን ስልጡንና ዘመናዊ ያደረገ፣ የወደፊት እድገታቸውን ያመለከተ፣ የሕዝብን የመልማት ፍላጎትና ቁጭት ያሳደገ ነው።
ከሪደር ልማት የስራ ባሕልንም የቀየረ፤ ለአዳዲስ ስራዎችም መነሳሳትን የፈጠረ፣ ተወዳዳሪነትን እያሳደገ፣ የከተሞችን ገጽታ የለወጠና ዘመናዊነትን ያላበሰ፤ የሕዝብን የአኗኗር ዘይቤና ባሕል በከፍተኛ ደረጃ እያሻሻለ ይገኛል።
ቀን ብቻ ከመሥራት ልምድ በማታ የመስራት ባሕልን አሳድጓል። ቀደም ባሉት ዓመታት ለግንባታ ሒደታቸው ዓመታትን የሚወስዱ የመንግሥትና የግል የልማት ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ጠብቀው በአጭር ጊዜ እንዲከወኑ እድል ተፈጥሯል።
ይሕ ስኬት የመንግሥት አዲስ እይታ ውጤት ነው። የመንግሥት አዲስ የልማት አተያይ፣ እቅድ እና ርዕይ በሕዝብ ዘንድም የላቀ ቁጭት ፈጥሮ ወደ ተጨባጭ ውጤት እየተቀየረ ነው።
ይህ የጋራ ቁጭትና መነሳሳት ደግሞ ለቀጣይ ክልላዊ እቅድ ስኬት፣ ልማትና እድገት መሠረት ይሆናል።
የመፈጸም አቅምን ከጊዜ ወደ ጊዜ ያሳድጋል፤ ልማት እና እድገትን ያፋጥናል። የከተሞችን ገጽታ ይቀይራል ፤ የልማት መሻትን ያሟላል፤የነገ ልማት እቅድ መዳረሻን ይበይናል። የሕዝብ ለልማት ተነሳሽነትን ይፈጥራል።
የመጪውን ትውልድ በዳበረ የስራ ባሕልና እሴት ያንጻል። ተዳዳሪና ዘመኑን የዋጁ ስልጡን ከተሞችን የመገንባት እቅድ፣ ርዕይና ሕልም እውን ያደርጋል።
የክልሉ መንግሥት በከተሞች የጀመረውን ዛሬን የመስራት እና ለነገ የተሻሉ ከተሞች መሠረት የመጣል እርምጃ በሁሉም ከተሞች አጠናክሮ ይቀጥላል።

