(ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም) የክልል እና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ መሪዎች “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ቱሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት በወቅታዊ ክልላዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በደሴ ከተማ ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አወሉ አብዲ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ፣ የከተማ አሥተዳደሩ እና የዞኑ መሪዎች በመድረኩ ተገኝተዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ ደሴ የኢትዮጵያዊነት መሠረት እና የአንድነት ተምሳሌት ከተማ ናት ብለዋል።
እንደ ሀገር ባዳ እና ባንዳ ሕዝብን በፈተኑበት ወቅት ሳይቀር ደሴ እና የአካባቢው ሕዝብ ሰላምን ለመጠበቅ ቁርጠኝነቱን ማሳየቱን አንስተው ለዚህም አመስግነዋል።
የጥፋት ቡድኖች የሕዝብን ኑሮ ለማወክ ሙከራ ቢያደርጉም ሕዝቡ ግን የተደገሰውን ጥፋት ቀድሞ በመረዳት ለሰላም ዋጋ ከፍሏል፤ ሰላሙንም አጽንቷል ነው ያሉት።
ለሰላም የተከፈለ ዋጋ ለሀገር እና ለሕዝብ የተከፈለ ዋጋ ነው፣ ለዚህም ምስጋና እና ክብር ይገባል ነው ያሉት።
ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ በሙሉ አቅም ልማቶችን ለመገንባት አሁንም ቢኾን ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
እንደ ሀገር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተበሠሩ የጉባ ብስራቶችን ጠቅሰው እነዚህ ትልልቅ የሀገር እና የሕዝብ ሕልሞች እውን እንዲኾኑ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
“የጉባ ብሥራቶቻችንን ተከታትለን እንፈጽማለን፤ ኢትዮጵያን እንደ ስሟ በከፍታ ላይ እናስቀምጣለን” ነው ያሉት አቶ ፍስሐ።
ሰላም ለልማት ወሳኝ መኾኑን ጠቅሰው በተለይም እስካሁን ድረስ ታጥቀው በጫካ ውስጥ ያሉ ወገኖች ፈጥነው ሰላምን እንዲፈልጉ አስገንዝበዋል።
ሕዝቡም ታጥቀው በጥፋት መንገድ እየተጓዙ ያሉ ልጆቹን መምከር እና ወደ ሰላም መመለስ አለበት ብለዋል።
የመንግሥት የምንጊዜም ምርጫ ሰላም ነው፤ ሰላም ጠል በኾኑት ላይ ደግሞ ሕግ ለማስከበር ይሠራል ብለዋል።
ሕዝቡ ሰላም ይስፈን፣ የትርክት ይሻሻል እና ልማት ይፋጠን የሚሉ ጥያቄዎች አሉት፤ መንግሥትም የሕዝቡን ጥያቄዎች ቆጥሮ ለመፍታት እየሠራ ነው ብለዋል።
በተለይም የሚያለያዩ ትርክቶችን ለማረቅ በጋራ የሚያስተሳስሩንን ደግሞ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የተጀመሩ ሥራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት አቶ ፍስሐ።
ደሴ ከተማ ስሟን በሚመጥን የኮሪደር ልማት እንድትደምቅ የተለያዩ ሥራዎች በተግባር እየተከናወኑ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ “ደሴ ሰላም፣ ፍቅር እና አብሮነትን እንደሸማ ፈትላ የያዘች አብሮ የመኖር አንጥረኛ ናት” ብለዋል።
ደሴ ኢትዮጵያዊነትን በጉያዋ አቅፋ የያዘች፣ በነባር እና ያልተበረዙ እሴቶቿ የታጀበ ኅብረብሔራዊ አንድነት እና ወንድማማችነትን እንደዝምድና ያጸናች ፈርጥ ናትም ብለዋታል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከሰቱ ግጭት አዙሪቶችን በመመከት እና ሀገርን ከጥፋት በመታደግ በኩልም እንደሌሎች አካባቢዎች ሁሉ የደሴ ከተማ ሕዝብም ታሪክ የማይረሳው ውለታ ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።
የደሴ ሕዝብ አስተዋይ፣ ሆደ ሰፊ እና አይበገሬ ሲኾን ሰውንም በሰውነቱ ብቻ ያከብራል ብለዋል ከንቲባው።
ደሴ ሃይማኖቶች በዝምድና ተጋምደው የሚኖሩባት፤ ነዋሪዎቿም የተናጠል እጣፋንታ እንደማያዋጣ ጠንቅቀው በመረዳት በጋራ እጣፈንታ ተሰናስለው የሚኖሩባት ስለመኾኗ ገልጸዋል።
ደሴን በማልማት ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ታልሞ እየተሠራ ስለመኾኑም ከንቲባው አንስተዋል።
በከተማው አቅም የልማት ድርጅት በማቋቋም ወጭን በሚቆጥብ አካሄድ የኮሪደር ልማት ሥራ ተከናውኗል፤ ተጨማሪም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከተማዋ ዘመናዊ እና ለዜጎች የተመቸ አገልግሎት የሚሰጥ የመናኸሪያ አገልግሎት ተገንብቶ ሥራ ላይ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የደሴ ሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ገበያን ለማረጋጋት የተገነቡ የገበያ ማዕከላት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እና ሌሎችም ልማቶች ቃል በተግባር የተፈጸመባቸው እና ሕዝብ የሚመሠክራቸው ናቸው ብለዋል።
ደሴ ከዚህም በላይ ልማት እንደሚያስፈልጋት ገልጸው ለዚህም ያለመታከት እየተሠራ ስለመኾኑ ጠቁመዋል ከንቲባው።
ሕዝቡ ሰላሙን እና አንድነቱን አጽንቶ፤ አልባሌ ውዥንብር የሚነዙ ግጭት ጠማቂዎችን ጆሮ ነስቶ ከሰላም እና ልማቱ ጎን መሰለፍ እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

