“ግብርና ለኢንደስትሪ ሽግግር ትልቅ አቅም እንዲኾን እየተሠራ ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

(ኅዳር 26/2018 ዓ.ም) ወንዳፍራሽ ጥላሁን ይባላሉ በሰሜን ሸዋ ዞን ሲያደብርና ዋዩ ወረዳ የአባያ ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው፡፡

በዚሁ ቀበሌ ሁለት ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የመኸር ስንዴ አልምተዋል፡፡

ከዓመት በፊት በሰው ኀይል ነበር ሰብላቸውን የሚሠበሥቡት።ጠ

አሁን ላይ ግን በኮምባይነር በመታገዝ ነው የስንዴ ሰብላቸውን ሢሠበሠቡ አሚኮ ያገኛቸው፡፡

በመኸር ዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም በተጨማሪ የተሻለ ምርት እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በወረዳው እየተከናወነ ያለውን የሰብል አሠባሠብ ሥራ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ጉብኝት ተደርጓል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ 800 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል የለማ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የድኅረ ምርት ብክነት እንዳይፈጠርም በኩታ ገጠም የለሙ ማሳዎች ኮምባይነር በመጠቀም እየተሠበሠቡ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ እየታየ ያለው የሜካናይዜሽን ፍላጎት ሰፊ እንደኾነ እና ይህም ለገጠር ትራንስፎርሜሽን ዕድገት ወሳኝ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ያሉት ዶክተር ድረስ 300 ኮምባይነር ለማሰራጨትም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ይህም ወደ ተግባር ለተገባበት የአሻጋሪ ዕቅድ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ግብርና ለኢንደስትሪ ሽግግር ትልቅ አቅም እንዲኾን እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ያለውን ሰፊ አቅም ለመጠቀም እየተሠራ ነው ያሉት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ በዞኑ 162 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ መልማቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 40 ሺህ ሄክታር የስንዴ ሰብል በኮምባይነር እየተሠበሠበ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም የአርሶ አደሮችን የሜካናይዜሽን ፍላጎት ለማሟላት እና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ አሠራሮችን በቁርጠኝነት ለመተግበር ይሠራል ነው ያሉት ሲል የዘገበው አሚኮ ነው፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top