“ቴክኖሎጂ መር አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረግን ነው” ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር)

(ኅዳር 25/2018 ዓ.ም) ፕላንና ልማት ቢሮ በለሙ ሶፍተዌሮች አጠቃቀም ዙሪያ ለርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪዎች ስልጠና ተሰጥቷል።

የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ የክልሉን ተቋማት የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አተገባበር ውጤታማነት በኃላፊነት የመከታተልና አፈጻጸማቸውን የመገምገም ስራ እያከናወነ ይገኛል።

ቢሮው የክልሉን ተቋማት ተግባር አፈፃፀም መሠረት አድርጎ የመመዘን ተግባርና ኃላፊነቱን በውጤታማነት ለመከወን የሚያስችሉትን የተለያዩ ሶፍትዌሮችን ከክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር አልምቶ ወደስራ አስገብቷል።

በለሙ ሶፍትዌሮች አጠቃቀም ዙሪያ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ነው፡፡

በቅርቡ አልምቶ ወደ ስራ ባስገባቸው የፕሮጀክት ማኔጅመንት አስተዳደር እና የተቋማት የአፈፃፀም ምዘና (KPI) ሶፍትዌሮች ዙሪያ ለክልሉ ርእሰ መስተዳድር አማካሪዎች ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናውን በንግግር ያስጀመሩት የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ.ር) የስልጠናው አላማ አማካሪዎች የሶፍዌሩን አጠቃቀም ተረድተው የክልሉን የእቅድ አፈጻጸም መረጃ እንዲያገኙና የእቅድ አፈጻጸሙን ተከታትለው እንዲደግፉ ለማድረግ መሆኑን አንስተዋል።

አማካሪዎች በወቅታዊ የክልሉ አቅድ አፈጻጸም ላይ ተመሥርተው የማማከር ተግባርና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቢሮ ሀላፊው አክለውም ከተለመዱ የማኑዋል አሰራሮች ለመውጣትና ቴክኖሎጂ መር አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ፕላንና ልማት ቢሮ ጥረት እያረገ ነው ብለዋል፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው የተሰጠን ስልጠና ሶፍተዌሮቹን አውቀን በመጠቀም የክልሉን የልማት አፈጻጸም በቴክኖሎጂ እንድንከታተል እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በክልሉ እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች እና ሌሎች የልማት ስራዎች ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ ተረድተን የማማከር ተግባርና ኃላፊነታችንን ለመወጣት አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ቢሮው እያለማው የሚገኘው ሶፍተዌር ከዘልማዳዊ አሰራር የወጣ እና ቴክኖሎጂ መር ክትትልና ድጋፍን የሚያጠናክር መሆኑን ሰልጣኞቹ በሰጡት አስተያየት አንስተዋል።

ክልሉ ያስቀመጠውን የ25 ዓመት የአሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት እቅድ በተቀላጠፈ መንገድ ለማስተግበር ሌሎች ተቋም አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች መውሰድ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top