(ኃዳር 24/2018) በአማራ ክልል የቱሪዝም ፀጋዎችን ለይቶ ወደ ስራ በማስገባት ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገቱ ያለውን አበርክቶ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለፁ።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በሆቴል ዘርፍ ለመሰማራት ቦታ ተረክበው በተለያየ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ባለሃብቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በወቅቱ እንዳሉት፤ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ በሀገር በቀል ብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ ትኩረት የተሰጠው ነው።
ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገቱ ያለውን አበርክቶ ለመወጣት የ25 ዓመት ፍኖተ ካርታ እና የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ ባለፉት ጊዜያት ለግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መሰጠቱንና በተሰራው ስራም ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚገባውን ያህል ትኩረት አለመሰጠቱን አስታውሰው አሁን ላይ ፀጋዎችን ለይቶ በማልማት ለኢኮኖሚ እድገቱ ሚናውን የበለጠ እንዲወጣ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የመስህብ ሃብቶችንና መዳረሻዎችን በማልማት ወደ ስራ እየተገባ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለዚህም የሆቴል አገልግሎትና የኮንፍረንስ ቱሪዝም መስፋፋት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተለይም በባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሀንና ሌሎች ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ወደ ስራ ለማስገባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚደረግ ጠቁመው ሃላፊነታቸውን በማይወጡ ላይ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ፕሮጀክቶቻቸውን ፈጥነው በማጠናቀቅ ለአገልግሎት በማብቃት ለዘርፉ እድገት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቦታ ወስደው ወደ አገልግሎት መግባት ባልቻሉ ባለሃብቶች ላይ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ሃላፊ ተሻገር አዳሙ ናቸው።
በዚህም ባለፉት ወራት ለ350 ፕሮጀክቶች ድጋፍና ክትትል መደረጉን አረጋግጠዋል።
በዚህም ወደ ተግባር መግባት ባልቻሉ 205 ፕሮጀክቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው፤ ለ60 ባለሃብቶች ተሰጥቶ የነበረ ቦታ መነጠቁንና ለ145 ለሚሆኑት ደግሞ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል።
የውይይት መድረኩ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች እየተሰጣቸው ያለውን እገዛ በመጠቀም ፈጥነው ወደ ስራ እንዲሰማሩ መግባባት ላይ ለመድረስ ታሰቦ የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ሞላ መልካሙ(ዶ/ር) የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ባለሃብቶች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

