(ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም ) “በመደመር መንግሥት እይታ፣ የዘርፎች እምርታ” በሚል መሪ መልዕክት ለከፍተኛ መሪዎች ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተጠናቅቋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ላይ የማጠቃለያ ሥልጠና ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማጠቃለያ ሥልጠናው ላይ የመሪዎች ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ፣ በፍጥነት እና በጥራት መሥራት ለሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በሥልጠናው የመደመር መንግሥት ፅንሰ ሀሳብ፣ መንገድ እና መዳረሻ ግቦቹ ተዳስሰዋል። በዚህም በመደመር መንግሥት መርሕ የሚመራው ፓርቲ መሪዎች በፈጠራ በፍጥነት በብዛት ሥራዎችን በማከናወን የሕዝባችን ሁለንተናዊ ጥያቄ ከመመለስ በላይ የሀገራችን ራዕይ ለማሳካት እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚረዳ መንገድ መምራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የ5 ሚሊዮን ኮደሮች፣ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች፣ የምርጫ ምቹነት እና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም አጀንዳዎችን ለማሳካት መትጋት እንደሚገባ አመላክተዋል።
መደመር ትውልድን ወደ ብልጽግና የሚያደርስ መንገድ ነው ብለዋል። የመደመር መንግሥት ለሀገር ብልጽግና ባለአደራ መኾኑንም ተናግረዋል። በፈጠራና በፍጥነት ጥራትና ብዛትን እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው
በብዝኃ ዘርፍ ትስስር ወደ ሥልጣኔ ሽግግር ማምጣት ይገባል ነው ያሉት።
የሀሳብ ሉዐላዊነት የብልጽግና መሠረት እንደኾነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም የፓርቲው መሪዎች በዚህ አግባብ በመትጋት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል።
የፓርቲው ከፍተኛ መሪዎች ባለፉት 11 ቀናት በሥልጠና፣ በውይይት፣ በመስክ ጉብኝት እና በማጠቃለያው ገለጻ ያገኟቸውን ዕውቀቶች፣ ልምዶች በዕቅድ በማካተት፣ ወደ ሥራ በመቀየር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

