(ጥቅምት 23/2018)፦ለጎንደር ከተማ እድገትና ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በጎንደር ከተማ የንግዱ ማህብረሰብ አባላት ገለጹ፡፡
በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችና በአካባቢ ሰላምና ልማት ዙሪያ የከተማው የንግዱ ማህበረሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ አካሂደዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አብዱራህማን ሰኢድ ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ዳር እንዲደርሱና ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በተለይም በአካባቢው የሰፈነው ሰላም ለማጽናትና የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ወጣቶችን መምከራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ተሾመ ንጉሱ በበኩላቸው፥ እንደ አንድ የንግዱ ማህበረሰብ አባል ህብረተሰቡን የሚያማርሩ ህገ ወጦችን በማጋለጥ መንግስት ለሰላም መስፈን የሚያደርገውን ጥረት ይበልጥ ለማገዝ እንደሚተጉ አስረድተዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ የግብር ግዴታውን በመወጣት ለሀገር እድገት የሚያበረክተውን ሚና ማጠናከር እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
በምንከፍለው ግብር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን በማየታችን ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻዬን ለማበርከት ዝግጁ ነኝ ያሉት ደግሞ አቶ ጀማል ቃሲም ናቸው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ጥሩዬ አታክልት እንደገለጹት፥ የከተማው ሰላም መረጋገጥ የንግድ እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ አስችሏል።
በዚህም የንግዱ ማህበረሰብ ሰርቶ በሚያገኘው ልክ የመንግስትን ግብር በታማኝነትና በወቅቱ እንዲከፍል ምቹ መደላድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
ይህም በግብር አወሳሰንና አከፋፈል የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመፍታትም መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎትን ለማስጀመር እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የንግዱ ማህበሰረብ አባላትም በሰላም ግንባታ እያበረከቱ ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡
በምክክር መድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከስድስት ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተሳታፊ ናቸው ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

