የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
በክልሉ የሚሰጡ ተልዕኮዎችን ለመወጣት እና ከፌደራል የጸጥታ ኃይል ጋር በሚናበብ መልኩ የፖሊስ ተቋም ሪፎርም እየተሰራ ነው አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።
አቶ አረጋ ከበደ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሪፎርም አካል የሆነ የዘመናዊ ህንጻ ምርቃት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በክልሉ ያለው የጸጥታ አካላት ሪፎርም የሀገር አቀፉ ሪፎርም አካል እንደሆነና የአደረጃጀትና አሰራር ለውጥ ማምጣትን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ከልል ፖሊስ ለክልሉ ሰላም እና አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከተ መሆኑን አንስተው÷ በዚህም ተልዕኮን መሰረት ባደረገ መልኩ አሰራሩን በመገምገም መሰራቱን ጠቁመዋል።
የክልሉን ፖሊስ አደረጃጀት በማስተካከል ብቁ እና ተልዕኮ ፈጻሚ እንዲሆን በአማራ ክልል ምክር ቤት ቀርቦ የፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ጸድቆ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
የክልሉ የሚሊሻ ኃይልም የሪፎርም ተግባር አካል ሆኖ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው÷ የጸጥታ ኃይሉ አቅም ሕዝብ በመሆኑ ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ ትኩረት ተሰጥተው እየተሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
በዛሬው የሪፎርም ሥራዎች ዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያ እና የአዲስ ሕንጻ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ፣ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ፣ የአማራ ክልል ዋና አፈጉባኤ ክብርት ፋንቱ ተስፋዬ፣ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኀላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሸነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ.ር)፣ ምክትል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የቢሮ ኃላፊዎች፣የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የጦር አዛዦች፣ የክልሉ ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ ስታፍ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።
