ከዓለም ጋር ሊያወዳድር የሚችል የአሠራር ሥርዓትን እና የመረጃ ጥራትን ማረጋገጥ ይገባል።

(መስከረም 18/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ስታስቲክስ የልማት ፕሮግራም ሥራዎች ዙሪያ ከአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) እና ሌሎችም የአማራ ክልል እና የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ መሪዎች እየተሳተፉ ነው።

የውይይቱ ዋነኛ ዓላማም ጠንካራ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ሥርዓትን በመዘርጋት እና የመረጃ ጥራትን በማስጠበቅ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

ውይይቱ በመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች አሥተዳደር፣ በዲጂታል የእቅድ ክትትል እና ግምገማ ሥርዓት፣ በክልል የኢኮኖሚ አካውንት እና በአመራር ቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ያተኮረ ነው።

በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት ዛሬ ውይይት የሚደረግባቸው ርእሰ ጉዳዮች በክልሉ ቀደም ብለው የተጀመሩ እና የበለጠ መጠናከር ያለባቸው ናቸው ብለዋል።

በተለይም የፕሮጀክት አሥተዳደር እና አፈጻጸምን በዲጂታል አሠራር ለመለካት ሶፍትዌር መልማቱን እና በአዋጅም መደገፉን ተናግረዋል። በቀጣዩ የምክር ቤቱ ጉባኤም አዋጁ ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ፕላን እና ልማት ሚኒስትር ለመወያየት ወደ ክልሉ ይዟቸው የመጡ ርእሰ ጉዳዮችም አማራ ክልል ከያዛቸው የልማት እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች ጋር የተጣጣሙ እና አጋዥም የሚኾኑ ናቸው ብለዋል።

ከክልል እስከ ፌደራል ድረስ ያለውን ተናባቢነት እና የጋራ ሥራም የሚያሳድግ ስለመኾኑ ጠቅሰዋል።

እንደ ሀገር የሚወጡ አሠራሮችን የክልሉም የለውጥ ሥራዎች አካል በማድረግ ለሕዝብ ጥቅም በሚያስገኝ መልኩ እንሠራለንም ብለዋል።

እንደ አማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ፣ የፖሊሲ ልማት ኢንስቲትዩት እና የመሳሰሉ አሥፈጻሚ አካላትም ሥራዎችን ቀድመው እያከናወኑ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድሩ ጠቁመዋል።

እነዚህን ሥራዎች የሚደግፍ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በቅርቡ መቋቋሙም ሥራዎችን ለመተግበር ቀላል ያደርገዋል ብለዋል።

ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴርም ተጨማሪ እገዛዎችን በማግኘት አሠራሮችን ለማላቅ እንሠራለን ነው ያሉት።

ከዛሬው ውይይት በኋላም ጥልቅ የኾኑ እና ቴክኒካል የኾኑ ድጋፎች እና የሥራ ክትትሎች እንደሚኖሩም ገልጸዋል። ክልሉ ለነዚህ ሥራዎች ተግባራዊነት የሚያግዙ አስፈላጊ በጀቶችን መድቦ እንደሚሠራም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) በፌደራል መንግሥት ደረጃ በተግባር ተፈትነው ውጤት ያመጡ አሠራሮች ወደ ክልልም መውረድ ስላለባቸው ወደ አማራ ክልልም ይዘን መጥተናል ብለዋል።

በመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች አሥተዳደር፣ በዲጂታል የእቅድ ክትትል እና ግምገማ ሥርዓት፣ በክልል የኢኮኖሚ አካውንት እና በአመራር ቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ውይይት በማድረግ ተጨባጭ ለውጦችን ለማምጣት የሚያግዝ ውይይት እና ተከታታይ ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን የዘላቂ ልማት ባለቤት ለማድረግ ከተፈለገ ከሌሎች የዓለም ሀገራት ሊያወዳድር የሚችል ጠንካራ የአሠራር ሥርዓትን መከተል ይገባልም ብለዋዋል ሚኒስትሯ። በተለይም ጠንካራ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ሥርዓት እና የመረጃ ጥራትን ማረጋገጥ ወሳኝ ተግባር ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር ከዚህ በፊት የነበረው የመንግሥት ኢንቨስትመንት አሥተዳደር ሥርዓት በርካታ ችግሮች የሚታዩበት እንደ ነበር የጠቀሱት ሚኒስትሯ በወጉ ባይታቀዱ የመሠረት ድንጋይ የሚጣልላቸው፣ ለፍሬም የማይበቁ ሕልም መሳይ ልማቶች እንደነበሩ አስረድተዋል።

ይህም በሕዝብ በኩል ቅሬታን ጭምር ሲያስነሳ ቆይቷል ነው ያሉት። ይህ አሠራር ከዚህ በኋላ አይቀጥልም፤ በሳይንሳዊ እቅድ እና በጠንካራ ክትትል የሚከናወኑ ልማቶች ብቻ ይከናወናሉ ነው ያሉት።

ሚኒስትሯ አማራ ክልል በውጣ ውረድ ውስጥ የቆየ ቢኾንም ለሀገር ኢኮኖሚ ጭምር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ልማቶችን ሲያከናውን እንደነበር አንስተዋል።

ክልሉ አሻጋሪ እቅድ አውጥቶ ለዘላቂ ልማት እየሠራ እንደኾነ እና ለዚህም ፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ተከታታይ ድጋፍ እንደሚያደርግም ዶክተር ፍጹም ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top