ሕዳሴ በአንድነት ማሳካት የማንችለው እንደሌለ ያሳየ ዳግማዊ ዓድዋ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

ሕዳሴ በአንድነት ማሳካት የማንችለው እንደሌለ ያሳየ ዳግማዊ ዓድዋ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

(መስከረም 06/2018) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ በባሕር ዳር ከተማ የድጋፍ እና የደስታ መግለጫ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።

በድጋፉ እና የደስታ መግለጫው ሰልፍ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የዘንድሮውን የዘመን መለወጫ ከድል ላይ ድል ተጎናጽፈን ያከበርነው ነው ብለዋል። ዓመቱ ቁርሾ የሚዘጋበት፣ ፍቅር እና አንድነት እንዲኾን እመኛለሁ ነው ያሉት።

ዛሬ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በደስታ ተውጠው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን እያከበሩት ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ክብሯን እና ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች፣ የራሷ ሥልጣኔ ያላት፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የታፈረች እና የተከበረች ናት ነው ያሉት። ኢትዮጵያ የነጻነት ባለቤት መኾኗን የማይፈልጉ ጠላቶች ሲገፏት እና ሲወጓት መኖራቸውን አንስተዋል። ኢትዮጵያውያን ግን ማሸነፍ ልምዳቸው ነውና ድል ሲያደርጉ ኖረዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በግጭት እና በድህነት አዙሪት ውስጥ መቆየቷንም አንስተዋል። አሁን ላይ ከድህነት እና ከግጭት ለማውጣት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የብልጽግና ጅማሮ መኾኑን አንስተዋል። ሕዳሴ የአሸናፊነት ማሳያ፣ የብልጽግና ጉዞ ማብሰሪያ፣ የአንድነት ማሳያ፣ በአንድነት ማሳካት የማንችለው እንደሌለ ያሳየ ዳግማዊ ዓድዋ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያሰበችውን እያሰካች ትቀጥላለች፤ የሚያቆማት የለም ነው ያሉት። የባሕር ዳር መሪዎች እና ነዋሪዎች ለሀገር የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል። ከተማዋን በዓለም ተወዳዳሪ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ባሕር ዳር ሰላም ናት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰላም እንዳልኾነች የምትናገሩ ሰዎች ይበቃል፤ ተው አቁሙ ብለዋል። ይልቅስ መጥተው እንዲዝናኑባት፣ እንዲጉበኟት እና እንዲያለሙባት ጥሪ አቅርበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች እስካሁን ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top