የአማራ ክልል ምክር ቤት ለ2010 በጀት አመት 37 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር አጸደቀ
የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ በ4ኛ ቀኑ የቀጣይ አመት በጀቱን አጽድቋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት በ7ኛ መደበኛ ጉባኤው ለ2010 በጀት አመት 37ቢሊዮን 693ሚሊዮን 142 ሺህ 155 ብር አድርጎ አጽድቋል፡፡ካለፈው አመትም 15 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
የአማራ ክልል የስነ-ህዝብ ጉዳዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ መካሄዱ ተገለጸ፡፡ ሀምሌ 12 ቀን 2009 ዓ.ም የአማራ ክልል የስነ-ህዝብ ጉዳዮች ምክር ቤት "የሰው ሃብት ልማት ለስነ-ህዝብ መልካም አጋጣሚ የላቀ ደረጃ ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ቃል መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ፡፡ ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአንድ አገር እድገት መሰረታዊ መለኪያ የህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ነው፣ የአንድ አካባቢ አገር ሊያሰኘው የሚችለው መሰረቱ ህዝብ በመሆኑ የስነ-ህዝብ ጉዳዮች ምክር ቤት አባላት በጉባኤው ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በድሉ ድንገቱ የክልሉ የስነ-ህዝብ ጉዳዮች ተግባራት አፈጻጸም ከስነ-ህዝብ ፖሊሲው አንጻር ያለበትን ደረጃ በሪፖርታቸው ገልጸው በክልሉ የውልደትና ሞት መጠን እየቀነሰ መጥቷል አማካኝ የመኖር ዕድሜ እየጨመረ ነው፤ የህዝብ ቁጥር የዕድገት ምጣኔም እንደ አሮፖያን ዘመን አቆጣጠር በ1994 ከነበረበት 3 በመቶ አሁን 1.74 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡ አቶ በድሉ እንደገለጹት በትምህርት፣በጤና እና በስርዓተ-ጾታ ጉዳዮች እድገት የታየ ሲሆን፤ በከተሜነት ምጣኔ ወደ ኋላ መቅረት ይታያል፤ ከጤናው ዘርፍ ጋር በተገናኘም የመቀንጨር ምጣኔ 46.3 በመቶ ነው ከሁሉም ክልሎች የበለጠ ነው ይህ በምክር ቤቱ አባላት በኩል በአሳሳቢነት የሚታይ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ በተያያዘም ለ4ኛ ጊዜ በሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ በክልል ያለውን ዝግጅት የሚያሳይ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ የምክር ቤት አባላትም አስተያየታቸውን አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል የስነ-ህዝብ ጉዳዮች ምክር ቤት በ2006 ዓ.ም በአዋጅ መቋቋሙ ይታወሳል፤ ከተቋቋመበት ጊዜ አንጻር እንቅስቃሴው የሚመሰገን ቢሆንም በቀጣይ ከዚህ በተሻለ መደራጀት እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ እንዲፀድቅ የውሳኔ ሃሳብ መቅረቡ ተገለጸ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 2ኛ አመት የስራ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2009 ዓ/ም ባደረገው አስራ ስምንተኛ መደበኛ ስብሰባ የኮምቦልቻ ከተማ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ እንዲያጸድቅ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረቡን ገለጸ፡፡
በአጀንዳው ላይ ውይይቱ የተጀመረው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ በሰጡት ማብራሪያ ሲሆን የኮምቦልቻ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት ረቂቅ የውሃ ታሪፍ በከተማ ውሃ አገልግሎቶች በኩል ተጠንቶና በቢሮው ታይቶ በመስተዳድር ምክር ቤቱ እንዲፅድቅ የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ቢሮ ኃላፊው እንደገለጹት የኮምቦልቻ ከተማ የውሃ ታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት አገልግሎት ጽ/ቤቱ ከመንግስት ድጎማ ሙሉ በሙሉ ተላቆ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማዳረስ የሚያስችለው የኦፕሬሽንና ጥገና፣ የኢንቨስትመንት፣የመስመር ማስፋፊያና ማሻሻያ ወጭዎችን በራሱ እንዲሸፍን ለማስቻል፣ ውስን የሆነውን የመጠጥ ውሃ ሀብትን በአግባቡና በቁጠባ ለመጠቀም፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቱን ዘላቂና አስተማማኝ በማድረግ የከተማዋን ህዝብ በማንኛውም ስዓትና ቦታ በቂና አስተማማኝ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እና ተቋሙ በተሟላና ብቃት ባለው ባለሙያ እንዲደራጅ ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ዘላቂ ማድረግ እንዲቻል ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረት ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያዬ በኋላ የኮምቦልቻ የመጠጥ ውሃ ታሪፍ ማሻሻያ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ማስተካከያዎች ተደርገውበት ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡ |
አዲስ የተከፈሉ 11 ወረዳዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መወሰኑ ተገለጸ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 2ኛ አመት የስራ ዘመን ሰኔ 16 ቀን 2009 ዓ/ም ባደረገው 22ኛ መደበኛ ስብሰባ አዲስ የተከፈሉ ወረዳዎችን ወደ ስራ ለማስገባት አስፈላጊውን ነገር ለማሟላት ውሳኔ መሰጠቱን አስታወቀ፡፡ ውይይቱ የተደረገው ሰብሳቢው በሰጡት የመነሻ ሀሳብ ሲሆን ባለፈው ዓመት በአዲስ ተደራጅተው በዚህ ዓመት የአስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብርና አፈ-ጉባዔ ጽ/ቤቶች አደረጃጀት ተፈቅዶላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው 11 ወረዳዎች በቀጣይ ከሀምሌ 1/2009 ዓ/ም በሙሉ አቅም ስራ መጀመር ስላለባቸው በጀታቸውም ከዚህ አኳያ ታይቶ በቀመር ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ በመሆኑ ወረዳዎቹ በተመጠነ ሁኔታ አደረጃጀት እንዲሰራላቸው ወረዳዎቹ ሲደራጁም በተመጠነና ጥቂት የሰው ኃይል እንዲይዙ በሚያደርግ አግባብ እንዲደራጁ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ መዋቅሩን አዘጋጅቶ እንዲያወርድና ፈጥነው ወደ ስራ የሚገቡበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ሆኖ የሚደራጁት ሴክተሮችም ዋና ዋና አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሆነው እንዲደራጁና አስፈላጊ ናቸው ተብለው የተፈቀዱ መደቦችን ባካተተ ሁኔታ መዋቅሩ እንዲሰራ ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ መሆኑን ቀርቧል፡፡
መስተዳድር ምክር ቤቱም በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ በቀረበው አቅጣጫ መሰረት የወረዳዎች መዋቅር በተመጠነ አግባብ ተሰርቶ ከሀምሌ 1/2009 ዓ/ም ጀምሮ 11ዱ ወረዳዎች በሙሉ አቅም ወደ ስራ እንዲገቡ እንዲደረግ ወስኗል፡፡ የግንቦት 20 በዓልን ምክንያት በማድረግ በይቅርታ እንዲፈቱ ለህግ ታራሚዎች ውሳኔ መሰጠቱ ተገለፀ፡፡ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 2ኛ አመት የስራ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ/ም ባካሔደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ ከ3000 (ሦስት ሽህ )በላይ የሚሆኑ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን ገለጸ፡፡ ውይይቱ የተጀመረው የፍትህ ቢሮ ኃላፊ የክልሉን የይቅርታ ቦርድ የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ በማብራራት ሲሆን በ2009 ዓ/ም የሚካሔደውን የግንቦት 20 የድል በዓል አስመልክቶ የ2ኛ ዙር የይቅርታ ተጠቃሚ በመሆን በክልሉ መንግስት ይቅርታ እንዲደረግላቸው በክልሉ ይቅርታ አቅራቢ ቦርድ ተጠንተው የተለዩ የህግ ታራሚዎች የይቅርታ መስፈርቱን አሟልተው ጥያቄ ካቀረቡት ታራሚዎች መካከል በየደረጃው በሚገኙ ሚኒ ካቢኔ ታይቶ በየቦርዱም የይቅርታ ጥያቄአቸው የተደገፉ በድምሩ 3275 ታራሚዎች በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ታይተው ለመስተዳድር ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ መሆኑን ገልፀው፣ በይቅርታ ቦርዱ ታይተው የውሳኔ ሀሳብ የቀረበባቸው የህግ ታራሚዎችን በዝርዝር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ስለዚህ መስተዳድር ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት በማካሔድ እርቅ የማይጠይቁ የወንጀል አይነቶች ተከሰው የተቀጡ የእስራትና የባህሪ ለውጥ መስፈርቶችን ያሟሉ በየደረጃው በለው ሚኒ ካቢኔ ታይቶ የቀረበና እንዲፈቱ የቦርዱንም ድጋፍ ያገኙ ወንድ=2501 ሴት=69 ድምር=2570 ፤ በሰው መግደልና በመግደል ሙከራ ተከሰው የተፈረደባቸው ከሟች ቤተሰብ ወይም ከግል ተበዳዩ ጋር ታርቀው የዕርቅ ሰነድ ያቀረቡ በየደረጃው ያሉ ሚኒ ካቢኔ ያረጋገጠው የቦርዱንም ይሁንታ ያገኙ ወንድ 674 ሴት 6 ድምር 680 ፤ እርቅ በሚጠይቅ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉትና ለመታረማቸው ማረጋገጫ ቀርቦላቸው ነገር ግን ታራቂ ወገን በክልሉ ውስጥ የሌለ መሆኑ የተረጋገጠ ወንድ 20 ሴት 3 ድምር 23 ፤ በጤና መስፈርቱ መሰረት የማይድን የጉበትና የካንሰር ታማሚ የሆኑና ለዚህ ማረጋገጫ ያቀረቡ ወንድ 1 ሴት የለም ድምር 1 ፤ በእድሜ መስፈርት እድሜአቸው 86 አመትና ከዚያ በላይ የሆኑና እንዲፈቱ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ወንድ 1 ሴት የለም ድምር 1
በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱ አቅጣጫዎችንና ማስተካከያዎችን በማካተት ወንድ 3197 ሴት 78 ድምር 3275 የህግ ታራሚዎችን ከግንቦት 20 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮ የይቅርታው ተጠቃሚ በመሆን ከእስር እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡ |