የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ፈንድ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ መውጣቱ ተገለጸ፡፡
የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን ህዳር 15 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ፈንድ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ መስጠቱን ገለጸ፡፡
የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሠፋ በላይ እንደገለጹት የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ፈንድ መቋቋም ያስፈለገበት በህብረተሠቡ ውስጥ ያለውን እርስ በርስ የመረዳዳት ባህል በማጎልበት በክልሉ ውስጥ ለሚከሰቱ ድንገተኛና አስቸኳይ የእርዳታ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት አደጋውን ለመቀነስና የሠው ህይዎትም ሆነ ንብረት ከጥፋት ለመታደግ ለሚያግዝ በቂ የሆነ የመጠባበቂያ ሃብት ክምችት ለመያዝ የሚያስችል ክልል አቀፍ ስርዓት ለመዘርጋት ነው ብለዋል፡፡
በፈንዱ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንቡ ላይ በየአንቀፁ የሠፈሩትን የፈንዱ ዓላማዎች፣ የገቢ ምንጮች፣ ስለ ፈንዱ አስተዳደር፣ አመራርና ተጠሪነት፣ ስለፈንዱ አጠቃቀም መመዘኛዎች፣ በፈንዱ ስለሚሠጥ ዕርዳታና ድጋፍ፣ ስለክልሉ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚቴ የአባልነት ጥንቅርና ተዋጽኦ እንዲሁም ሌሎች በደንቡ የተካተቱ ሃሳቦችን በዝርዝር በማቅረብ፣ ረቂቅ ደንቡ በክልሉ ፍትህ ቢሮና በርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የህግ አማካሪ በተገቢው መንገድ ታይቶ የቀረበ በመሆኑ መስተዳድር ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ መክሮ ረቂቅ ደንቡን እንዲያፀድቅላቸው ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡
መስተዳድር ምክር ቤቱም ከቀረበው ማብራሪያ በማንሳት በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችንና በማነሳት ሠፊ ውይይት ካካሄደ በኋላ፡- በየጊዜው አደጋ ሲደርስ ሃብት የማሰባሰብ ስራ ከመስራት አደጋ ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ ለመከላከል ታስቦበት ራሱን የቻለ ከመንግስት፣ ከለጋሽ ድርጅቶች፣ ከግለሰቦች ለአደጋ መከላከል የሚሆን ሃብት ማሰባሰብ የሚያስችል ፈንድ ሊቋቋም እንደሚገባ በማመን የቀረበው የአብክመ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ፈንድ ማቋቋሚያ ደንብ የመስተዳድር ም/ቤቱ ደንብ ሆኑ እንዲወጣ በሙሉ ድምፅ ተወስኗል፡፡
ታህሳስ 25/2010 ዓ.ም
የዳያስፖራና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት
የጣና ሀይቅና አካባቢ ደህንነት ፈንድን ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ ደንብ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ/ም ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባው የጣና ሀይቅና አካባቢ ደህንነት ፈንድ ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ ደንብ ማውጣቱን አስታወቀ፡፡ የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውንና ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን መጤ አረም ለመከላከልና ለማጥፋት የሚውል ሀብት ስለሚያስፈልግ ይህንን ሀብት በአግባቡ ለመሰብሰብ የሚያስችል ህጋዊ ደንብ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ በረቂቅ ደንቡ ላይ በየአንቀጹ የቀረቡትን ዝርዝር ጉዳዮች ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ መስተዳድር ም/ቤቱም ከቀረበው ማብራሪያ በመነሳት የተለያዩ ሀሳቦችንና አስተያየቶችን በማንሳት ሰፊ ውይይት ካካሔደ በኋላ የጣና ሀይቅ ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ ወደፊት መመለስ የማይቻል ጥፋት ሊያስከትል ስለሚችል ይህንን አስቀድሞ ለመንከባከብ መደገፍ የሚፈልጉ ሀይሎች ስላሉ የፈንዱ መቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ ላይ በመስማማት፤ የአባይ ተፋሰስ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ፣ የክልል ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር፣ የክልል ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር፣ የክልሉ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት እና በርዕሰ መስተዳድሩ የሚሰየሙ ከ3 ያልበለጡ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የስራ አመራር ቦርድ አባል ሆነው እንዲካተቱ፤ ለተፋሰሱ እንክብካቤ የገንዘብ አስተዋጽኦ ማድረግ ለሚፈልጉ ማናቸውም የህብረተሰብ ክፍሎችና ድርጅቶች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ቋሚ የበጀት ቋት ማደራጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከመንግስት፣ ከህብረተሰቡ፣ ከግል ሴክተሩ፣ ከምርምርና ትምህርት ተቋማት የተውጣጣ በበላይነት የጣናን ፈንድ የሚያስተዳድር ተጠያቂነት ያለው በቦርድ የሚመራ ፈንድ የተቋቋመ መሆኑን ለህብረተሰቡ በሚዲያ መግለጽ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡ የጣና ደህንነት ፈንድ ጽ/ቤት እስኪቋቋምና ስራ እስኪጀምር ድረስ አካባቢ ደንና ዱር እንስሳ ጥበቃ ባለስልጣን የሚያደራጁት አካውንት እንዲከፈት ማድረግ ሀብቱን የማፈላለግ እና የተሰበሰበውን ሀብት ስራ ላይ የማዋልና ሌሎችን ስራዎች በኃላፊነት ይዞ ከወዲሁ መስራት እንዳለበት በመስማማት የጣና ሀይቅና አካባቢ ደህንነት ፈንድ ደንብ ለክልሉ ም/ቤት ቀርቦ ከፀደቀበት ከጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ወስኗል፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሰራተኞችና አመራሮች 10ኛውን የሰንደቅ ዓለማ ቀን በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡ በምክትል ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ ደረጃ የዳያስፖራና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ማስሬ "የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግልና ሀገራዊ ህዳሴያችን" በሚል ርዕሰ ጉዳይ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በፓናል ውይይቱ የተገኙት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ያየህ አዲስ ሰንደቅ ዓላማ የአንድ አገር ህዝቦች የማንነት መገለጫ ሲሆን በአንድ ወቅት ከፍ ወዳለ የስልጣኔ ማማ የወጣቸው ሀገር በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረ አለመረጋጋት የኢኮኖሚ ድቀት የድህነት መገለጫ ሆና ቆይታለች ብለዋል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ከነበረችበት የቁልቁለት ጉዞ ወደ ዕድገት ማማ እየገሰገሰች ያለች ሀገር መሆን ችላለች ያሉት አቶ ያየህ አዲስ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም ብዝሃነትን በማስተናገድ በኩል በአለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ሀገር መሆን ችላለች ሰንደቅ አላማዋም ከፍ ብሎ መውለብለብ ጀምሯል ብለዋል፡፡ አክለውም ይህን ክብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ሁሉም በተሰማራበት የስራ ዘርፍ ውጤታማ ስራ በመስራት አባቶቻችን ያስተማሩን ለሰንደቅ አላማ መስዋዕትነት መክፈል አዲሱ ትውልድ የሰንደቅ አላማን ፋይዳ እንዲረዳ በማድረግ ድህነትን በማሸነፍ ሰንደቅ አላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ከተገኙት ተሳታፊዎች መካከል አቶ መርሀጽድቅ መኮነን እና አቶ ሞገስ አያሌው እንደተናገሩት ትውልዱ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መርሆችና እሴቶች አንግቦ እና ሰንደቋን ጨብጦ አገሩን ቀጣይነት ወዳለው ከፍታ ማማ እያወጣት ይገኛል፤ ዋነኛ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማሸነፍ በተያያዝነው ጠንካራ ትግል የህዝቦች የአንድነት ህብረቀለም ሆና እያገለገለች ያለችውን ይህቺው ሰንደቅ ዓላማችን በመሆኗ ልንጠብቃት፣ ልንንከባከባትና አስፈላጊም ከሆነ የህይወት መስዋዕትነት ልንከፍልላት የምትገባ ቅርሳችን ናት ብለዋል፡፡ |
ከኦሮሚያና ከሶማሊያ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ተሰጠ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው 7ኛ መደበኛ ስብሰባ ከኦሮሚያና ሶማሌ ክልል በርዕስ በርስ ግጭት ለተፈናቀሉ ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ይቻል ዘንድ ድጋፍ እንዲሰጥ መወሰኑን ገለጸ፡፡ መስተዳር ምክር ቤቱ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በወቅቱ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በተፈናቀሉ ወገኖች ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ እነዚህን ወገኖች ለማቋቋምና ለመደገፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የክልሉ መንግስት የችግሩን አስከፊነት በመረዳት 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ገልጿል፡፡
መስተዳር ምክር ቤቱ ከችግሩ ስፋት አንጻር የድጋፍ መጠኑ እንደ ክልል የሚወሰን ቢሆንም በሀሳብ ደረጃ ከሌሎች ክልሎች ጋር ምክክር የተደረገ መሆኑንና ገንዘቡም በፌደራል ድጋፉን አማክሎ ለሚያሰባስበው አካል ገቢ የሚደረግ መሆኑን እና ከሁለቱም ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ የሚውል ብር 10 ሚሊዮን በፌደራል ደረጃ ድጋፉን ለሚያስተባብረው አካል ገቢ እንዲደረግ መስተዳድር ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡ የአማራ ክልል መንግስት ከሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ጋር በንግድ፣ ልማትና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ዙሪያ ላይ ውይይት ማካሄዱ ተገለጸ፡፡ የአማራ ክልል መንግስት ከሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ዋና አስተዳዳሪ እንጂነር መርጋኒ ሳሊህ እና በዋና አስተዳዳሪው የሚመራው የሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በንግድ፣ በልማትና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ዙሪያ ላይ በባህር ዳር ተገኝተው ውይይት ማካሔዳቸውን የአብክመ ርዕሰ መስተዳድር አሳወቀ፡፡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክክር መድረኩ እንደተናገሩት የገዳሪፍ ግዛት ከፍተኛ የልዖካን ቡድን እና የአማራ ክልል አቻው ከሁለቱ ጎረቤት ሀገሮች አልፎ በዓለም አጀንዳዎች ሊመክር የሚገባው በመሆኑ በዋናዋና ጉዳዮች ላይ ግልጽና አጭር ውይይት በማድረግ ሁለቱን ቀጠናዎች የሚጠቅሙ የቀጣይ አቅጣጫዎችን ጭምር ማስቀመጥ ይገባናል ብለዋል፡፡ አቶ ገዱ አያይዘውም የሁለቱ ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረና የቆየ ወዳጅነት ያለው በመሆኑ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ትንንሽ ችግሮች የሁለቱም ግዛቶች አመራሮች በውይይት ሊፈቱት የሚገባ እንጅ ወደ ከፋ ነገር ሊሄድ አይችልም ብለዋል፡፡ የሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር መርጋኒ ሳሊህ ሳይድ አህመድ በበኩላቸው ልማታችሁ ጥሩ እየሄደ መሆኑን እናደንቃለን በተለይ በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰራው ስራ ማሳያ ነው ካሉ በኋላ በሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት እና በአማራ ክልል በኩል ያለው ግንኙነት ጥሩ መሆኑን ገልጸው በትምህርት፣ በጤና፣ ነጻ ገበያ ለማቋቋም በሚኖረው የነጻ ገበያ ልውውጥ ነጻ እንዲሆን፣ ህገ- ወጥ የንግድ ልውውጥ እንዳይኖር ማንኛውም ችግር እንዳይፈጠር ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል፡፡ ዋና አስተዳዳሪው አክለውም በሁለቱም አካባቢ ጥሩ የሆነ ግንኙነት ስላለ የሽርክና ማህበር ለማቋቋም እንፈልጋለን፣ በእናንተ በኩል ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልግ ካለ እንፈቅዳለን እኛ ወደ እናንተ ኢንቨስት ለማድረግ ፈቃደኛ ነን በማለት ገልጸዋል፡፡ በዋና አስተዳዳሪው የተመራው ልዑካን ቡድን የገዳሪፍ ፖሊስ አዛዥ ፣ የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊ እና የደህንነት ኃላፊው ጀኔራል መሀመድ ጦይብ በኢትዮጵያ እየተሠሩ ያሉ ልማቶች እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ የሁለቱ ቀጠናዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ታሪካዊና በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በመሆኑም በደንበር አካባቢ በተለይ ከአርሶ አደሩ ጋር የሚያጋጥመንን አለመግባባቶች አመራሮች በግልጽ ተወያይተን አቅጣጫ አስቀምጠን ግንኙነታችን በልማትና የሁለቱን ቀጠናዎች ጥቅሞች በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
|
- የአማራ ክልል አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ፡፡
- በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የቤት መስሪያ ቦታ አሰጣጥ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ውሳኔ መሰጠቱ ተገለጸ
- የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሠራተኞችና አመራሮች በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና በወቅታዊ የበሽታው ስርጭት ዙሪያ ውይይት አደረጉ
- የሶማሊያ አገር ከፍተኛ አመራሮችና የምክር ቤት አባላት በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መዲና ባህርዳር በፌዴራሊዝም ስርዓት ዙሪያ የልምድ ልውውጥ አካሄዱ፡፡