የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

የርዕሰ መስተዳድርና ክልል መስተዳድር

ምክር ቤት /ቤት

 

በአማራ ክልል የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማጎልበት የክልሉ

መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው

 

 

 

አዘጋጅ፡-

አውላቸው ማስሬ

የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች አስተባባሪና የሕዝብ ግንኙነት ዋና

የስራ ሂደት መሪ

መጋቢት / 2004 .

ባህር ዳር

 

 

 

በአሁኑ ሰዓት የክልሉ መንግስት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በክልላቸው በተለያዩ የልማት መስኮች የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆን የሚደረገውን ድጋፍ ለማጠናከር እንዲቻል ርዕሰ መስተዳድርና ክልል መስተዳድር ም/ቤት ጽ/ቤት የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡

1.   ዳያስፖራው ወደ ክልሉ መጥቶ እንዲያለማ  ለማድረግ መረጃዎችን  በተለያዩ መንገዶች  እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ዳያስፖራው በክልሉ ውስጥ በተለያዩ የልማት መስኮች እንዲሳተፍ ቅድሚያ መረጃዎችን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡መረጃው የሚሰጠው ወደ ክልላቸው ገብተው እንዲያለሙ፣ ስለክልላቸው  እንዲያውቁና እውቀታቸውን እንዲያስተላልፉ ለማድረግ ነው፡፡ አንዳንድ ዳያስፖራዎች የተሳሳተ መረጃ በየግለሰቡ ስለሚሰበስቡና ከሚመለከተው አካል ትክክለኛውን መረጃ ጠይቀው ስለማይወስዱ  ወደ ክልሉ ሲመጡ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ይህንን ችግር ለመቅረፍና ትክክለኛ መረጃ እንዲደርሳቸው ለማድረግ የተለያዩ አማራጮችን እንጠቀማለን፡፡ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ በየጊዜው ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ወቅታዊ መረጃዎችን ሰብስቦ በማደራጀት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚልክ ሲሆን ሚኒስቴር መ/ቤቱም ለሚሲዮኖች በመላክ ዳያስፖራው በኤምባሲዎች በኩል እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ወደ ኤምባሲዎች ቢሔዱና ድረ ገጽ ቢመለከቱ ማንኛውንም የአገር ውስጥ መረጃ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ እኛም በክልላችን ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያሳዩና ሌሎች መረጃዎችን በድረ ገጽ እናስቀምጣለን፡፡ አስፈላጊና ወሳኝ ጉዳዮች ሲኖሩም በሚዲያ መግለጫ እንዲሰጥባቸው እናደርጋለን፡፡

 

2. ዳያስፖራው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታዎች አሉ፡፡

ክልሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለውጭ ዜጐችም ጭምር ለኢንቨስትመንት ምቹ ሲሆን በክልሉ ውስጥ ባለሃብቶችና ዳያስፖራዎች ሊሰማሩባቸው የሚችሉ 200 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ፕሮፋይል በጥናት እንዲለዩ ተደርጓል፡፡ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንትም ሆነ በንግድ በሚሳተፉበት ጊዜ እንደ አገር ውስጥ ኢትዮጵያዊ እንዲቆጠሩ ለማድረግ መንግስት የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች እንዲዎጡ አድርጓል፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሚሰማራበት ኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራ ላይ መሳተፍ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን ለማድረግ ትውልደ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጸውን ቢጫ ካርድ መያዝ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል በውጭ አገር ሲኖሩ ያካበቱት ሀብት በውጭ ገንዘብ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው በገንዘቡ ለመንቀሳቀስ ችግር እንዳይገጥማቸው መንግስት የዳያስፖራ ባንክ አካውንት የሚከፍቱበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጀመሩት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ጋር የተያያዙ ዕቃዎችም ሲኖሩ እንደ አስፈላጊነቱ እየታየ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በኩል እየተረጋገጡ ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ በማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ በኩልም ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታና መንግሥት ለእያንዳንዱ ዘርፍ በሚያደርገው ድጋፍና ማበረታቻ ዙሪያ ገለጻ ይደረግላቸዋል፡፡ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ ወደ ክልላቸው ሲመጡ ተገቢውን ድጋፍና አገልግሎት በመስጠት ልናበረታታቸው ይገባል፡፡የኢንቨስትመንት ሥራ የአንድ ሴክተር ስራ ብቻ ባለመሆኑ የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡

3.  የዳያስፖራው ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ተገቢውን አገልግሎት/ምርት እንዲሰጡ ለማድረግ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት በክልሉ ውስጥ ለ273 የዳያስፖራ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን ያስመዘገቡት የካፒታል መጠንም 8.2 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ ሁሉም ፕሮጀክቶች ወደስራ ከገቡ ለ76,872  ለሚሆኑ ዜጐች ቋሚ የሥራ እድል እንዲሁም ለ127,218 ዜጐች ጊዜያዊ የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሁሉም ዞኖች የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው ከነዚህ ኘሮጀክቶች መካከል በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት/ምርት መስጠት የጀመሩት 53 ኘሮጀክቶች ናቸው። ዳያስፖራው በብዛት የሚመጣባቸው አገሮችም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ፈረንሣይ ናቸው፡፡

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው በበርካታ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ቢወስዱም ወደ ሥራ የገቡት ፕሮጀክቶች ግን ጥቂት ናቸው፡፡ አብዛኛው ዳያስፖራ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማውጣት ችግርማያጋጥመው ቢሆንም  ፡-

Ø  የተወሰኑ ዳያስፖራዎች በተሠጣቸው የኢንቨስትመንት ቦታ ላይ ለማልማት ያላቸው ፍላጐትና አቅም አናሳ መሆን (የተቀበሉትን ቦታ ለሌላ አካል ለማስተላለፍ መሞከር፤ ፈጥኖ ወደ ስራ አለመግባትና አጥሮ ማስቀመጥ)

Ø  በመንግስት በኩል ፕሮጀክቶቹ ወደ ተግባር እንዲገቡ ለማድረግ የሚሰጠው ድጋፍና የሚደረገው ክትትል  አናሳ መሆን የሚሉት ከሚስተዋሉት ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ እንደየፕሮጀክቱ አይነት ከሚመለከታቸው ሴክተር መ/ቤቶችና የስራ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት እንዲፈቱ እየተደረገ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በማንኛውም ጊዜ ወደ ውጭ ሀገር በሚሄዱበት ጊዜ ዳያስፖራውን በማወያየት በኢንቨስትመንቱ እንዲሳተፍ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለዳያስፖራው ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ባላሀብቶች ጭምር ትክክለኛ ልማታዊ ባለሀብት ስለመሆናቸው እየተረጋገጠ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲሰጥ የሚል አቅጣጫ በመቀመጡ አብዛኛዎቹ ወደ ተግባር እየገቡ ናቸው፡፡

3.  በሕዳሴው  ግድብ  የዳያስፖራው ተሳትፎ  እየጨመረ ነው፡፡

በ2003 ዓ.ም  ከሚያዚያ ወር ጀምሮ ለተከታታይ  ወራት  ሚኒስትሮች፣ የፌዴራልና የክልል ቢሮ ኃላፊዎች በአሜሪካ፣በካናዳ እንዲሁም በለንደንና ፍራንክፈርት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በሕዳሴው ግድብና በዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ እቅድ ዙርያ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ከውይይቱ በኋላ የዳያስፖራው አመለካከትና ለአገሩ ልማት ያለው ተነሣሽነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በሕዳሴው ግድብ ላይ አሻራውን ለማስቀመጥ በአንድ ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ፡፡ በዶላር፣ በዩሮና በፓውንድ የሚሸጡ ኩፖኖችም በተለያየ መጠን ታትመው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለዳያስፖራው እየተሰራጩ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ዳያስፖራው ከ5.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለግድቡ ድጋፍ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰጠው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

4. ዳያስፖራው ከገንዘብና ከተለየዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ባሻገር በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እየተሳተፈ ነው፡፡

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ላይ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ የተለያየ እውቀት፣ ክህሎትና ሙያ ያላቸው ዳያስፖራዎች በአገር ውስጥ ገብተው በውጭ ቆይታቸው ያካበቱትን እውቀትና ልምድ እንዲያካፍሉ መንግስት ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው፡፡ በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል  የክፍተት ዳሰሳ ጥናት የተካሄደ ሲሆን በዳሰሳ ጥናቱም የክህሎት ክፍተቶች ተለይተው ለሚሲዮኖች ተላልፈዋል፡፡ በተለዩት የሙያ ክፍተቶች መሰረት እውቀት ያለው ዳያስፖራ ወደ ክልሉ ዩንቨርስቲዎች መጥቶ እንዲያገለግል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

4.  የዳያስፖራውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማጠናከር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት የዳያስፖራ ረቂቅ ፖሊሲ አዘጋጅቷል፡፡

ዳያስፖራው በትውልድ አገሩ የሚያደርገውን ተሳትፎ በተደራጀ ሁኔታ ለማሳደግና ለማጠናከር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት የዳያስፖራ ረቂቅ ፖሊሲ ያዘጋጀ ሲሆን ፖሊሲውም በሰኔ ወር 2004 ዓ.ም ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

LatestNews

Who is online

We have 346 guests and 7 members online