የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የካቲት 7/2006 ዓ.ም ባካሄደው 4ኛ ዓመት 15ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲን ማቋቋሚያ ደንብ አውጥቷል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ ጉዳዩ ሠፊ ትንታኔ እና እይታ ይኖረው ዘንድ ረቂቅ አጀንዳውን ለህግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ በመምራት ከፍተኛ ምክክር ከተደረገበት በኋላ ነው በዚሁ እለት ቋሚ ኮሚቴው የደረሰበትን የውሳኔ አስተያየት በንባብ ከሰማ በኋላ ውሳኔ ያሳለፈው።

ቋሚ ኮሚቴው ደንቡ የፌድራል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጅን መሠረት በማድረግ ክልላዊ ባህሪይ እንዲኖረው ተደርጐ የተዘጋጀ መሆኑና ክልሉ ካለው ስፋትና የህዝብ ብዛት አንፃር ኩነቶችን ማለትም ከልደት፣ ከጋብቻ፣ ከፍች እና ከሞት እንዲሁም ከሌሎች ኩነቶች ጋር በተያያዘ የምዝገባ ሥራ በተደራጀ መንገድ በመስራት ዋነኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን የክልሉ ህብረተሰብ በኢኮኖሚ፣በማህበራዊና ለፍትህ አስተዳደሩ አጋዥ እና ጠቃሚ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ዓላማ ያለዉ መንግስታዊ ተቋም እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ የልማት አጋዥ መሆኑን አመላክቷል።

መስተዳድር ም/ቤቱም በጉዳዩ ላይ ሠፊ ውይይት፣ ጥያቄና መልስ በማድረግ በደንቡ መውጣት ላይ በመስማማት የክልሉ ውሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በኤጀንሲ ደረጃ ራሱን ችሎ እንዲቋቋምና ተጠሪነቱም ለፍትህ ቢሮ እንዲሆን ወስኗል።

በተጨማሪ ኤጀንሲው ምክር ቤት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተመልክቷል። የቦርድ አባላቱም የፍትህ ቢሮ ኃላፊ፣ የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ የኤጀንሲው ዳይሬክተር እና ሌሎች የሚመለከታቸው ምክትል ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሆኑ ተወስኗል።

LatestNews

Who is online

We have 319 guests and 8 members online