(ኅዳር 28/2018 ዓ.ም) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በሚዲያ እና የተግባቦት ሥራዎች ላይ ከአጋር አካላት ጋር ተወያይቷል።
የተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የተካሄደው የውይይት መድረክ ተባብሮ በመሥራት ሕዝብን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው።
በውይይት መድረኩ አሚኮ በሚዲየሞቹ ለኅብረተሰብ ለውጥ የሚያከናውነውን የሚዲያ ሥራ አጋር አካላት በውል ተረድተው መረጃን በተፈለገ ጊዜ መስጠት እንደሚገባቸውም ተነስቷል።
የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ቀልጣፋ እና ተዓማኒ የኾነ መረጃን ለሕዝብ የማድርስ ኀላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ለሁለንተናዊ ልማትና የኅብረተሰብ ተጠቃሚነት አሚኮን በአግባቡ መጠቀም እንደሚፈልግ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዎችም የሚዲያውን ሥራ ማገዝና ማስተባበር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
አሚኮ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ለሚሠራው የዘገባ ሥራ የታዩ ያለመተባበር ውስንነቶች መስተካከል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዎች ተቋማቸው ለሕዝብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ሚዲያውን በውጤታማነት መጠቀም እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ለተግባሩ ውጤታማነትም አሚኮ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ለመስጠት ዝግጁ ነው ብለዋል።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተግባራትን በእቅድ በመምራትና ተቀናጂቶ በመሥራት ማሳካት እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን ከአሚኮ ጋር ተባብሮ የመሥራትን ሥራ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በየጊዜው እየተገናኙ መመካከር፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ተቋማት የማኅበረሰብን ችግር የሚፈታ የሚዲያ ሥራ መሥራት የሚቻልበት ሰፊ እድል እንዳለም አመላክተዋል፡፡
የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ዘመኑን የሚመጥን ቀልጣፋ እና ተአማኒ መረጃ ለሕዝብ በማድረስ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል
የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዎች በየተቋማቸው ለሚዲያ መረጃ በመስጠት በኩል የሚታዩ ውስንነቶችን በማረም መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያውን አቅም ለመገንባት በቀጣይ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

