“ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚሠራ ኀይል ለሕዝብ አይጠቅምም” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

(ኅዳር 28/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከደብረ ወርቅ ከተማ አሥተዳደር እና ከእናርጅ እናውጋ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በአማራ ክልል በተሠራው ሥራ አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል፤ ነገር ግን አሁንም በርካታ ችግሮች አሉ፤ እንዲስተካከሉ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በስፋት ማምረት እና ነጻ የንግድ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፤ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ሰላምን ማረጋገጥ ይጠበቃል ነው ያሉት። የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ ሰላማቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ መነጣጠል አያስፈልጋትም፤ ከፋፋይ እና ነጣጣይ ትርክት አያስፈልግም በማለት ገዢ ትርክት ላይ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጣዊ ባንዳዎች ጋር በመኾን ኢትዮጵያ በሀብቷ እንዳትጠቀም ለማድረግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የተሰለፈ፣ እሴት እና ባሕልን የሚያጠፋ፣ የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን የሚያዋርድ እና የሚገድል ነው ብለዋል። መንግሥት ችግሮች እንዲቋጩ በሆደ ሰፊነት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መሥራቱን ተናግረዋል።

ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ሁሉንም የሰላም አማራጮችን ተጠቅመናል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን አቅርበናል፤ በቀረበው የሰላም ጥሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል ነው ያሉት።

በቅርቡ ደግሞ ለዘላቂ ሰላም የሰላም ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል። አሁንም ሰላማዊ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንስተዋል።

ከሰላም አማራጮች ባሻገር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከልብ መምከር እና መወያየት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። መሪዎች የሕዝብ አንድነትን ለማጠናከር እና ልማትን ለማረጋገጥ እንዲሠሩም አሳስበዋል።

ከአማራ ሕዝብ እና ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚሠራ ኀይል ለሕዝብ አይጠቅምም፤ ጠላት ነው ብለዋል።

የሕዝብ ሰላም በተራ ሽፍታ እና ባንዳ ሊደናቅፍ እንደማይገባውም ተናግረዋል።

ከልባችሁ ለሰላም ከተነሳችሁ ሰላማችሁን ታረጋግጣላችሁ ነው ያሉት። ሚናቸውን ለይተው ሰላማቸውን እንዲያረጋግጡም አሳስበዋል።

እናንተ ባሕሮች ናችሁ፣ ታጣቂ ቡድኑ ደግሞ አሳ ነው፤ ለባሕሩ ደኅንነት ሲባል አሳውን ማውጣት አለባችሁ፤ ያን ጊዜ ሰላም ይረጋገጣል ነው ያሉት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top