“የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች የከተማውን ሰላም ከማስጠበቅ በተጨማሪ በልማት ስራዎችም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነዉ” ርእሰ መስተዳደር ክቡር አረጋ ከበደ

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አረጋ ከበደ በወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና መልካም አስተዳደር ስራዎች ዙሪያ ከባህርዳር ወጣቶች ጋር ዉይይት አካሂደዋል።

የከተማው ወጣቶች ክልሉ ግጭት ውስጥ በገባበት ከሀምሌ መጨረሻ 2015 ዓ/ም ጀምሮ አካባቢያቸውን በመጠበቅ፣ በግጭቱ ተሳታፊ ባለመሆን፣ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸዉን የተናገሩት ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ለአብነትም የባሕርዳር የኮሪደርና የጣናዳር ልማት፣ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልገሎት፣ ሰፋፊ የአስፓልት መንገዶች እንዲሰሩ እያደረጉት ላለዉ ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ወጣቶች በከተማዋ ሁሉን አቀፍ ስራዎች በእውቀታቸው፣ በገንዘብ እና በጉልበታቸው የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል ።

በቀጣይም ከመንግሥት ጎን በመሆን የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳድር ስራዎችን በመደገፍ እና በመስራት፣ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ በባለቤትነት እንዲሰሩ፣ ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ በልማት ስራዎች እንዲሳተፍ እንዲያደርጉ እና የወጣትነት ሚናቸውን እንዲወጡ ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ አሳስበዋል።

የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ የተከበሩ አቶ ጎሹ እንዳላማው እንደገለፁት የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ተግባራት በከተማ አስተዳድሩ መከናወናቸውን ገልጸው ፣በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስበዋል ፡፡

በሌላ በኩል የከተማው ወጣቶች ደግሞ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት መዋቅር ጋር በቅንጅትና በትብብር በመስራት፣ የከተማውን ሰላም በመጠበቅ፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ፣ በየ ደረጃው የሚነሱ የመልካም አሰተዳድር ጥያቄዎች እና የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደሎች እንዲስተካከሉ በማድረግ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top