“ሰላም እንዳይመጣ የሚፈልገው በግጭት የሚጠቀም ብቻ ነው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)

(ኅዳር 27/2018 ዓ.ም) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከመርጡለ ማርያም ከተማ አሥተዳደር እና ከእነብሴ ሣር ምድር ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ “ዘካሪ፣ መካሪ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተካሄደው።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዕዝ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን “እኛ ወደ እናንተ የምንመጣው ሰላምን ለማረጋገጥ ነው፤ ሌላ ተልዕኮ የለንም” ብለዋል።

በጠመንጃ የሚመለስ ጥያቄም ኾነ የሚረጋገጥ ልማት እንደሌለም ገልጸዋል። በጫካ የሚገኙ ጽንፈኞች የያዙት መንገድ ትክክል አይደለም፤ ሀገር እና ሕዝብ እየጎዳ ነው፤ በቃ ልትሏቸው ይገባል ነው ያሉት።

የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ግፊት እንዲያደርጉም አሳስበዋል። በአንድነት ኾነው ሰላማቸውን እንዲጠብቁም አስገንዝበዋል። ሕዝብ አንድ ኾኖ ለሰላም ሲነሳ የሚያቅተው ነገር እንደሌለም አንስተዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገር ሰላም እና ሕዝብ የሚቆም የሀገር መከታ መኾኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እና ፍላጎቶቿን ለማረጋገጥ የውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ ጠላቶች የሚጠነክሩት የውስጥ አንድነት ሲጠፋ ነውም ብለዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው የዕድገት መንገዶች ያልተዋጠላቸው፣ የኢትዮጵያ ዕድገት የማያስደስታቸው ታሪካዊ ጠላቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት እንዲሰፋ ይፈልጋሉ ነው ያሉት።

የውጭ ጠላቶችን ተልዕኮ በተሸከመው ጽንፈኛ ቡድን ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት የአማራ ሕዝብ የደረሰበት ግፍ በየትኛውም ዘመን አልደረሰበትም፤ በብዙው ተጎድቷል ብለዋል።

አሁን ላይ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለክልሉ የጸጥታ ኀይል እና ለክልሉ ሕዝብ ምሥጋና ይግባቸውና የተሻለ ሰላም ተፈጥሯል ነው ያሉት። የተሻለ የልማት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

የአማራን ሕዝብ ጥያቄ እናስመልሳለን በሚል ማደናገሪያ የተነሳው ቡድን ሕዝብን በእጅጉ መጉዳቱን ተናግረዋል።

ሕዝብን በማሰቃየት የሚፈታ የሕዝብ ጥያቄ እንደሌለም ገልጸዋል። ልጆቻችሁ ከትምህርት እንዲርቁ ያደረጉትን፣ መንገድ ላይ የሚዘርፉትን በቃችሁ ልትሉ ይገባል ነው ያሉት። ምሥራቅ ጎጃም ዞን በግጭቱ ምክንያት በትምህርት ዘርፉ መጎዳቱንም ተናግረዋል።

ጽንፈኛው ኀይል ሕዝብን ከማሰቃየት የዘለለ የሚያስመልሰው ጥያቄ የለም፤ መሽቶበታልም ብለዋል።

በበርካታ አካባቢዎች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ የሚገቡት በርካቶች መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የመንግሥት የመጀመሪያ ምርጫ የሰላም አማራጭ ነው፤ በተሰጠው የሰላም አማራጭ በርካቶች ገብተዋል፤ ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ የሰላም አማራጭን በማይቀበሉት ግን የሕግ ማስከበር ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።

ተደራጅተው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁም አስገንዝበዋል። ሰላማቸውን በዘላቂነት የሚጠብቁት ራሳቸው እንደኾኑም ገልጸዋል።

ሰላም እንዳይመጣ የሚፈልገው በግጭት የሚጠቀም ብቻ ነው ያሉት አስተባባሪው በግጭት እየተጠቀመ ሰላም እንዳይመጣ የሚሠራውን ማጥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ሕዝብን በአግባቡ ማገልገል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top