የፖሊስ ሠራዊቱ ሕብረ-ብሔራዊ አስተሳሰብን በመላበስ ለሚያገለግለው ሕዝብ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ።

(ኅዳር 27/2018 ዓ.ም) በወሎና በሸዋ ቀጠና ሲሰጥ የቆየው የጂኦስትቴጂካዊ እና የአመራር አቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።

በማጠቃለያ መርኃ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ ክልሉ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም ፖሊስ ችግሮችን ለመቀልበስ እና ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።

ክልሉን ሰላም የሚነሱ ሕገ-ወጥ አካላትን ከሕግ ማስከበር ተግባር ጎን ለጎን በሕዝብ ግንኙነት ሥራ የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ ሕዝብ ሰላም እንዲረጋገጥ ሁሉም አካል መረባረብ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።

በማጠቃለያ መርሀ-ግብሩ የስራ መመሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ.ር) “የምናስከብረው ብሔራዊ ጥቅም እና የምናገለግለው ሕዝብ አለን” ብለዋል።

ኮሚሽነሩ ለምናገለግለው ሕዝብ እና ለገባነው ቃል እንዲሁም ሙያዊ ሥነ-ምግባር የሚመጥን ተግባር መወጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የፖሊስ ሠራዊቱ ከአልተገቡ ተግባራት በመራቅ፣ ከክልል የተሻገረ ሕብረ-ብሔራዊ አስተሳሰብን በመላበስ ለሙያውና ለሚያገለግለው ሕዝብ ዋጋ እና ክብርን ባጎናጸፈ መልኩ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል የሀገራችንን ሰላም የሚያውኩ አካላትን በጋራ በመመከት በኩል የክልሉ የጸጥታ ኃይል ሚና ጉልህ መሆኑን አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አበበ ውቤ ስልጠናው መነቃቃትን የፈጠረ እንዲሁም የተጀመረውን የለውጥ ስራ ተረድቶ ተግባራዊ ለማድረግ ሰራዊቱ ባለቤትነት ተሰምቶት እንዲከውን ያስችለዋል ብለዋል።

ከስልጠናው የተገኘውን እውቀት ተጠቅመን የክልሉን ሕዝብ ሰላም ማረጋገጥ ይኖርብናል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ የተጠናከረ የወንጀል መከላከል ስራ ለመስራትም ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ተግባራትን መከወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የስልጠና ተሳታፊዎችም በበኩላቸው ስልጠናው የተቋሙን የከፍታ ዘመን ጉዞ መረዳት የሚያስችልና ለቀጣይ ተግባራት አቅምን በማጎልበትና በሀገራችን ጂኦስትቴጂካዊ ቁመና ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ክልሉ ከገጠመው የጸጥታ ችግር እንዲወጣ እና ስኬታማ የሕግ ማስከበር ሥራን ለመከወን ስልጠናው እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የስልጠናው ተሳታፊ የፖሊስ አመራርና አባላትም በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደርና በደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን እና ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።

በስልጠናው ድጋፍ ላበረከቱ አካላትም የእውቅና እና የሽልማት መርሀ-ግብር ተካሂዷል።

በመጨረሻም ሰልጣኞች ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት እና ቃለ መሀላቸውን በማደስ ስልጠናው መጠናቀቁን ከአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top