“የዳበረ ታሪክ፣ ባሕል እና ሃይማኖት ካለው ሕዝብ ግጭትን በምክክር መፍታት ይጠበቃል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከመርጡለ ማርያም ከተማ አሥተዳደር እና ከእነብሴ ሣር ምድር ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።

ውይይቱ “ዘካሪ፣ መካሪ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላምና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተካሄደ የሚገኘው።

በውይይቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዕዝ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ መርጡለ ማርያም የጥንት ታሪክ ባለቤት፣ የታላላቅ ሊቃውንት እና አባቶች መገኛ መኾኗን ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት ግን ውድመት እና የኢኮኖሚ መቀጨጭ ያስከተለ ችግር ገጥሟት ቆይቷል ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡ በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ፣ በነጻነት እንዳያለማ፣ ልጆቹ እንዳይማሩ፣ ነግዶ እንዳያተርፍ ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት። አሁን ላይ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የጸጥታ ኃይል እና በአካባቢው ማኅበረሰብ ሰላም ወዳድነት ወደ አንጻራዊ ሰላም ተሸጋግሯል ብለዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሁላችንም የመፍትሔው አካል መኾን መቻል አለብን ነው ያሉት። የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ሌሎችም የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችም ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እንዲመክሩ እና እንዲዘክሩ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሕዝብ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል። ግጭት አትራፊ አይደለም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በምክክር እና በመደማመጥ ሀገርን መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት።

የገጠመውን ችግር በንግግር እና በውይይት መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል። የዳበረ ታሪክ፣ ባሕል እና ሃይማኖት ካለው ሕዝብ ግጭትን በምክክር መፍታት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። አለመመካከር እና አለመወያየት ሀገርን እና ማኅበረሰብን ይጎዳል ነው ያሉት።

ሀገርን እና ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ችግሮችን በውይይት እየፈቱ መሄድ እንደሚገባም ተናግረዋል። ለሀገር በቀል ዕውቀት ቦታ መስጠት ይገባል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ባለፉት ዓመታት የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን የማያከብር፣ እሴትን እና ባሕል የሚጥስ ችግር ገጥሞ ቆይቷል ነው ያሉት።

የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአማራ ክልልን በምጣኔ ሃብት ወደ ኋላ እንዲቀር እንዳደረገው ነው የተናገሩት። የሰዎች እና የምርት ነጻ እንቅስቃሴ መገደቡንም ገልጸዋል። የሰዎች እና የምርት እንቅስቃሴ መገደብ ደግሞ የኑሮ ውድነት እና ሌሎች ችግሮች እንዲከሰቱ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት።

ባለፉት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች ከትምህርት ገበታ መራቃቸውን እና በትውልድ ላይ ስብራት የሚፈጥር ችግር መፈጠሩን ነው የገለጹት። ክልሉ የተማረ ትውልድ እንዳይኖረው የሚያደርግ ችግር መኾኑንም ተናግረዋል። ግጭቱ ውስጣዊ አንድነት እንዳይዳብር፣ ልማት እንዳይፋጠን ማደረጉንም አመላክተዋል።

ሕዝብ እየጎዳ ያለውን ችግር በውይይት እና በንግግር መፍታት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top