(ኅዳር 27/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ”ትውልድን በሥነ ምግባር፤ ተቋምን በአሠራር” በሚል መሪ መልዕክት ሲያከብር የቆየውን 22ኛውን ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን የማጠቃለያ መድረክ አካሂዷል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሐብታሙ ሞገስ በዓሉን ከማክበር ባለፈ ሙስና በሀገራችን ያስከተለውን ሁለንተናዊ ጉዳት ሁሉም ሕዝብ አውቆት ለጸረ ሙስና ትግሉ ቁርጠኛ እንዲኾን ለማድረግ ነው ብለዋል።
በሥነ ምግባር ያልታነጸ ትውልድ ሀገርን ማሻገር እንደማይችል እና ለብልሹ አሠራር እና ሙስና ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል።
ለዚህም ከቤተሰብ ጀምሮ ማኅበረሰቡ፣ ሲቪክ ማኅበራት እና የመንግሥት ተቋማት ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የተደረጉት ማሻሻያዎችን ውጤታማ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎትን ማቀላጠፍ እንደሚገባ አንስተዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ሠራተኞቹ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ብልሹ አሠራርን እንዲታገሉ አሳስበዋል።
ለትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ እና የጸረ ሙስና ትግልን ሁሉም ኅብረተሰብ በመተባበር ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቻምላክ ገብረማርያም በአማራ ክልል አገልጋይነትን ለማቀላጠፍ ትልቅ ዓላማ ተይዞ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በሀገር ግንባታ ትልቅ ሚና ያለውን የተቋም ግንባታ ለማጠናከር የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር በሥነ ምግባር ለመቃኘት ትልቅ ዓላማ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የተቀላጠፈ ዘመናዊ እና ተጠያቂነት ያለውን አገልግሎት ለመስጠት የዲጂታል አገልግሎትን በአንድ ማዕከል ለመስጠት ተጀምሮ ከ45 ቀን በላይ እንዳለፈው ገልጸዋል።
በዚህም ከ13 ሺህ በላይ አገልግሎቶች መሰጠታቸውን ጠቅሰዋል። ከዚህ የበለጠ አገልግሎት በመስጠት የሕዝብ እርካታን መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል። የኅብረተሰብ እርካታ እየታየበት መኾኑንም አውስተዋል።
አገልግሎቱን በማስፋት በአምስት የሪጂኦፖሊታን ከተሞች ወደ ሥራ እንቅስቃሴ ገብቷል ነው ያሉት። አገልግሎቱን በሌሎች መካከለኛ ከተሞች ለማስፋትም በእንቅስቃሴ ላይ መኾኑን ገልጸዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መጀመር ብቻ ሳይኾን በሥነ ምግባር የማገልገል አስፈላጊነትንም አንስተዋል።
ትውልድን በሥነ ምግባር በማነጽ አገልጋይነትን ለማጠናከር በብዙ ውጣ ውረዶች ታልፎ ውጤት እየተመዘገበ መኾኑን ያነሱት ወይዘሮ ባንቻምላክ ትውልድን በሥነ ምግባር የመገንባት ጉዳይ ትኩረት እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
የትውልድ ግንባታ እና ሙስናን የመታገል ጉዳይ የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አመራር እና ሠራተኞች ብቻ ሳይኾን ሁሉም አካል የሚመለከተው እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ተግባሩን ሁሉም አካል ሊደግፈው እና ለውጤታማነቱ ሊረባረብ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በውይይቱ ከባሕር ዳር የአንድ ሞሰብ አገልግሎት እና የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሠራተኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በሥነ ምግባር ግንባታ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በሙስና ላይ የመወያያ ጽሑፍ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

