ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የልማት ሥራዎችን ጎበኙ።

(ሕዳር 22/2018 ዓ.ም) በጉብኝቱ ከርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደብረ ማርቆስ እየተገነባ የሚገኘውን ዘመናዊ ሆስፒታል፣ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) እያስገነባው የሚገኘውን ሕንጻ እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ነው የጎበኙት።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ የከተማዋን እድገት እና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ባለቤትነት እየተገነባ የሚገኘው ሆስፒታል በመጠናቀቅ ላይ መኾኑን ተናግረዋል።

በመንቆረር ኮንስትራክሽን ድርጅት ተቋራጭነት የሚገነባው ሆስፒታሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ አልጋዎች ያሉት፣ ለደብረ ማርቆስ እና አካባቢው ሕዝብ ሰፊ አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብለዋል። በሽታን ለመከላከል እና አክሞ ለማዳን በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አንስተዋል።

ሆስፒታሉ ለከተማዋ ተጨማሪ አቅም እንደሚኾንም ገልጸዋል። እስከ ሚያዝያ 2018 ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ በሌላ ተቋራጭ ይሠራ እንደነበር እና ረጅም ጊዜ መውሰዱን ያስታወሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የመንቆረር ኮንስትራክሽን ከተረከበው በኋላ ግን በፍጥነት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ባለቤትነት እየተገነባ የሚገኘው ሕንጻም በመጠናቀቅ ላይ መኾኑን ተናግረዋል። ሕንጻውን የመንቆረር ኮንስትራክሽን እየገነባው መኾኑን ተናግረዋል።

በፍጥነት እየተሠራ የሚገኘው ግንባታው ባሕላዊ እና ታሪካዊ ይዘቶችን እንደያዘም ገልጸዋል። ግንባታው በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። በከተማዋ የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ ሰላሙን እየጠበቀ ወደ ልማቱ እየዞረ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዚህ ዓመት ከማኅበረሰቡ ጋር በመኾን በርካታ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት አቅደናል ነው ያሉት። የተጀመሩ ይጠናቀቃሉ፤ ሌሎች አዳዲስ የልማት ሥራዎችም ይሠራሉ ብለዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ሌሎች ሥራዎች ትኩረት እንደሚደረግባቸውም ተናግረዋል።

የከተማዋን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። የሕዝብን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ሥራዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

ከተማዋ ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋች ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የሕዝብን ጥያቄ መሠረት ያደረጉ እና የከተማዋን እድገት የሚመጥኑ የልማት ሥራዎች ይሠራሉ ነው ያሉት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top