(ኅዳር 22/2018 ዓ.ም) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በምሥራቅ ጎጃም ዞን
የአዋበል ወረዳ እና ሉማሜ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝቡን ለከፋ ውድቀት ዳርጎት ቆይቷል ብለዋል። ከወገን ዘመድ ጋር በሀዘን እና በደስታ እንዳንገናኝ ኾነናል፤ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል፤ አርሶ አደሮች በባለሙያ እንዳይደገፉ ተደርጓል ነው ያሉት።
ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት በቅንጅት መሥራት፣ ያልጠራውን መዋቅር ማጥራት እና ቁርጠኛ መኾን ይገባል ብለዋል። ከግጭት እና ከጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለም፤ “ትርፍ ያለው ከሰላም ብቻ ነው፤ ሰላምን በአንድነት ማጽናት ይገባናል ነው” ያሉት።
የውስጥ አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያ ያጣችውን የባሕር በር ማስመለስ እንደሚገባ ገልጸዋል። የውስጥ ችግሮችን በሰላማዊ አማራጮች እና በውይይት መፍታት እንደሚገባም አንስተዋል።
በአጭር ጊዜ ከአንጻራዊ ሰላም ወደ አስተማማኝ ሰላም መሸጋገር ይገባል፤ ከዚህ በላይ በሰላም እጦት ውስጥ መቆየት አይገባም ነው ያሉት።
የሰላም ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመፍታት ተወዳዳሪ ክልል መፍጠር ይገባናል፤ እኛ በግጭት ውስጥ እየኖርን ሌሎች በልማት ጥለውን እየሄዱ ነው፤ ከዚህ አዙሪት በፍጥነት መውጣት አለብን ነው ያሉት።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ልጆቻችን አልተማሩም ያሉት ተወያዮቹ በዚህ ከቀጠልን ነገ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባ ተማሪ አይኖረንም፤ ክልሉን የሚመራ መሪም አይፈጠርም ብለዋል። ወደ ኋላ ላለመቅረት ሰላምን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመመለስ እና የትምህርት ስብራቱን መጠገን ይገባል ነው ያሉት።
ሰላም በእጃችን ስንይዘው ቀላል ነው፤ ስናጣው ግን ዋጋ ከፍለንበታል ብለዋል።
እውነትን የተናገረ እየታፈነ እና የተሰቃየ መኾኑንም ተናግረዋል። በሕዝብ ላይ የሚጨክኑ አሉ፣ ሊበቃ ይገባል፤ ለሰላም በጋራ መሥራት እና ከችግር መውጣት ይገባናል ብለዋል። ለሰላም ሲባል የሚከፈለውን መስዋዕትነት መከፈል ይገባል፤ ያለ ሰላም መኖር አይቻልም ነው ያሉት።
በሁሉም ቀበሌዎች ላይ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን አስተማማኝ ሰላም መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል። ወደ ጫካ የወጡ ኃይሎችን እየመከሩ እና እየገሰጹ መመለስ ያስፈልጋል፤ ይህ ካልኾነ ግን ሕግ ማስከበር ይጠበቃል ነው ያሉት።
ያለ ሰላም አርሶ መጉረስ፣ ነግዶ ማትረፍ እና ተምሮ መለወጥ እንደማይቻልም ተናግረዋል። የእርስ በእርስ ግጭት ለዚህ ዘመን እንደማይመጥን እና አውዳሚ መኾኑንም ገልጸዋል። መገዳደል እና እርስ በእርስ መጠፋፋት ሊበቃ እንደሚገባም አንስተዋል።
የችግሩ መቋጫ እና የሰላም ማረጋገጫው ውይይት መኾኑንም ተናግረዋል። የጸጥታ ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዝርፊያ እና ሥርቆት እየተስፋፋ መኾኑንም ገልጸዋል። በጦርነት የሚነግድ እና ሃብት የሚያፈራ ይኖራል፤ ነገር ግን ጦርነት አብዛኛውን ሕዝብ እና ሀገር ይጎዳል ነው ያሉት።
የራሳችንን ችግር የምንፈታው እኛ ነን፣ ማንም መጥቶ ሊፈታልን አይችልም፤ ከጦርነት የሚያተርፉ በጦርነት እንድንቆይ የሚፈልጉ አሉ፣ ነገር ግን በአንድነት በቃ ልንል ይገባል ነው ያሉት። በለው፣ ውጋው ከሚል አስተሳሰብ በመውጣት ሰላም ይሁን፣ አንድነት ይምጣ፣ ፍቅር ይደርጅ ማለት ይገባል፤ ሀገራችን በግጭት አንጉዳት ብለዋል።
ከሰላም መረጋገጥ ባለፈ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱም ጠይቀዋል። የሉማሜ ከተማ የውኃ ችግር እንዲፈታም አንስተዋል። ከልማቱ በፊት ግን ሰላምን እንሻለን ነው ያሉት።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በሕዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን እንፈታለን ብለዋል። ከመንግሥት ተልዕኮ ውጭ ሕዝብን የሚያንገላታ ባለሙያ እና መሪ ላይም እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል። ጥያቄዎችን ለመፍታት እና ልማትን ለማረጋገጥ የሕዝብ ድጋፍ እና ትብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በአልባሌ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ሕዝባችን ተጨማሪ ሃብት እንዳያፈራ እና ያለውን ንብረት እንዲያጣ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል። በጫካ ውስጥ ያሉ ታጣቂዎች ብቻ ሳይኾን በከተማ ተቀምጠው ግጭት የሚያባብሱ ሰዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
በቅንጅት ከሠራን እና ለራሳችን ሰላም በጋራ ከቆምን ሰላምን ማረጋገጥ እንችላለን ነው ያሉት። ሌብነትን እና ሕገ ወጥነት መከላከል እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አሉ፤ በየደረጃው እንዲፈቱም በጋራ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሩ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን በንግግር እና በውይይት ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ውይይቶች እስከ ቀበሌ እና መንደር ድረስ መውረድ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብን ሰላም ለመመለስ እየሠራ ነው፤ ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ ደግሞ መወያየት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሠራዊቱ ከሕዝብ የወጣ፣ ለሕዝብ የሚሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የእናንተ የኾነው ሠራዊት እየደገፋችሁ ለራሳችሁ ሰላም መሥራት ይገባችኋል ነው ያሉት። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ዋና ተልዕኮው እንዲመለስ ሰላማችሁን መጠበቅ አለባችሁ ብለዋል።
በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች በሰላም እንዲገቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፤ አሁንም የሰላም አማራጭ ዝግ አልኾነም፤ የሰላም አማራጭን መቀበል ይገባቸዋል ነው ያሉት። ውይይትን የሚገፉ እና በተሳሳተ የትግል ስልት ያሉ ኃይሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ከተሳሳተ የትግል ስልት መውጣት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ የሚያደርግ አካሄድ ለሕዝብ እና ለሀገር እንደማይጠቅምም ተናግረዋል። የአማራ ልጆች እንዳይማሩ በማድረግ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መፍታት አይቻልም ነው ያሉት።
ሀገርን ለማፍረስ ከሚሠራ ባዕድ እና ባንዳ ጋር መተባበር እንደማይገባም አሳስበዋል። ሕዝብን ለችግር እየዳረገ ያለውን አልባሌ ድርጊት ማውገዝ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የሰዎችን የመናገር፣ የመኖር እና የመንቀሳቀስ መብት የሚከለክለውን የተሳሳተ አካሄድ መታገል ይጠበቅባችኋልም ብለዋል።
በነጻነት ለመንቀሳቀስ እንድትችሉ ሰላማችሁን ለማረጋገጥ መሥራት ይገባችኋል ነው ያሉት። ግጭት በቃን ተውን ልትሏቸው ይገባልም ብለዋል።
ሀሰተኛ ቅስቀሳዎችን በንቃት እና በጥንቃቄ መመልከት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ከጥቃቅን ችግሮች በመውጣት ማሳካት የምትፈልጋቸው ታላላቅ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉ፣ እነዚህን ታላላቅ ጉዳዮችን ለማሳካት የውስጥ ችግራችንን መፍታት እና በአንድነት መቆም አለብን ነው ያሉት።
ከጦርነት የሚገኝ ጥቅም እንደሌለ በውል መረዳት እንደሚገባም አሳስበዋል። ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመኾን ለሰላም እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።

